የብዙ ጥንዶች የፍቅር ግንኙነት በውስልትና ምክንያት ተቋርጧል

ህይወት ከውስልትና በኋላ

 

 

የብዙ ጥንዶች የፍቅር ግንኙነት በውስልትና ምክንያት ተቋርጧል፣ ቤተሰብ ተበጥብጦ ልጆች ተበትነዋል፤ ሆኖም ግን በእንደዚህ ዓይነት ከባድ የፍቅር ግንኙነት አደጋ ውስጥ ለማለፍ ጥቂት ጥቆማዎች  ብሎ ሳይኮሎጂ ቱደይ የተባለው ድህረ-ገጽ ያወጣውን አንድ ጽሑፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል መልካም ንባብ፡-

  • ከእኔ ምን ጎድሎባት ነው ሌላ ሰው ጋር የሄደችው የሚለውን ጥያቄ እራስህን ጠይቅ ምናልባትም ጉዳዩን በተሻለ መንገድ መረዳት ትችል ይሆናል፡፡

 

  • ወዲያው ወደ ማኅበራዊ ድህረ-ገጾች በመሄድ ያደረሰብሽን በደል እና ጉዳት፣ ጭካኔውን በንዴት እና በስሜት ተገፋፍተሸ ይፋ አታድርጊው፤ ምላሾችሽ በሙሉ በተቻለ መጠን ከስሜታዊነት የጸዱ እና ማስተዋል የታከለባቸው ይሁኑ፡፡
  • በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ለማሰብ እንኳን የሚከብድ ቢመስልህና ፈጽሞ አይሞከርም ብትልም እንደው ምናልባት ያሁኑን በደልና ጉዳት ይቅር ብዬ ይቅርታ አድረጌላት አብረን እንቀጥል ይሆናል ብለህ አስብ፤ ለዚህም ያመችህ ዘንድ ለሁሉም ጓደኞችህ እና ቤተሰብ ያለውን በሙሉ ዝርግፍ አድርገህ አትንገር ምክንያቱም ከይቅርታ በኋላ ለሚመጣው ህይወት ተጽእኖ ሊያሳድሩብህ ይችላሉ፡፡
  • ከላይ ለሁሉም ቤተሰቦችሽ እና ጓደኞችሽ መናገር ጥሩ ውጤት አይኖረውም ቢባበልም  ግን ሚስጥርሽን ልታጋሪው የምትችይው ሁነኛ የልብ ወዳጅ ያስፈልግሻል፡፡ ከዛ በኋላ ያለው ግንኙነትሽ ተስተካከለም አልተስተካከለም የልብሽን የምታዋይው፣ስሜትሽን የምትገልጭለት እና ጭንቀትሽን የምተነፍሽበት አንድ ሰው ያስፈልግሻል፤ ግን ይሄን ሰው በጥንቃቄ ምረጪ፡፡
  • ባንድ ጊዜ ወስነህ ሁሉን ነገር ጠቅለህ አትውጣ፤ በአንድ ጣሪያ ስር እንኳን ቆይተህ በአጽንኦት ማሰላሰል ካቃተህ ለተወሰነ ጊዜ የሆነ ቦታ ሁን እና ከስሜት በጸዳ መልኩ ጉዳዩን እያወጣህ አውርድ፡፡
  • በቀል ነገሮችን አያስተካክልም፡፡ ስሜታዊ እና አካላዊ የሆነ ጥቃቶችን ለጎዳን ሰው መሰንዘር ወደፊት ለሚኖራችሁ ግንኙነቶች (በነበራችሁም ነገር ላይ ለመቀጠል ወይም እንደ ጓደኛ ለመሆን) ችግር ይፈጥራል ስለዚህ ከእነዚህ መራቅ አስፈላጊ ነው፡፡
  • በማኅበራዊ ድህረ-ገጽ ላይ የጎዳሽን ሰው አትከታተይው ሲንግል ብሎ ጽፏል ወይስ በግንኙነት ውስጥ ነው፣ ማን ታግ አድርጋዋለች፣ የማንን ፎቶ ወድዷል ማንስ ላይ ኮሜንት አድርጓል እና የመሳሰሉ ነገሮችን አትከታተይ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች የጊዜ እና ጉልበት መጨረሻዎች ናቸውና ተያቸው፡፡
  • ልጆች ካሏችሁ ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ አድርጉ፤ አንቺን ሊበድልሽ ፣ ሊያዛንሽ እና በላይሽ ላይ ሄዶ ሊሆን ይችላል ሆኖም ግን ለልጆቹ አሁንም አባታቸው ነው ስለዚህ ስለ እርሱ የምታወሪው ነገር አነሱን እንዳይጎዳ ጥንቃቄ አድርጊ፡፡
  • በእነዚህ ነጥቦች ብቻ ህይወት እንደበፊቱ ትቀጥላለች ብለን መደምደም አንችልም፤ ከውስልትና በኋላ ግንኙነት ሊቀጥል ይችላል ካልሆነም ዓይንህ/ዓይንሽ ላፈር ሊባልም ይችላል፡፡ በመጨረሻም እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲፈጠሩ  ለእራሳችን ከማዘን እና እራሳችንን መውቀስ ትተን በበለጠ እራሳችንን ለመረዳት በቂ ጊዜ እና አማራጮች እንስጥ;፡፡

ምንጭ፡-zepsychologist

 

  

Related Topics