የእውቅና መድረክ

 

Image result for ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጎርጊስ

 

የተወለዱት እዚሁ አዲስ አበባ በ1917

ዓ.ም. ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን

የተከታተሉት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት

ሲሆን፣ ባገኟቸው የውጭ አገር የትምህርት

ዕድሎች በአየር ትራፊክ ፍሰት ላይ ያተኮሩ

ትምህርቶች ተምረዋል:: ትምህርታቸውን

አጠናቅቀው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ

በ1936 ዓ.ም. በገነት ውትድርና ትምህርት

ማዕከል የሚሊተሪ ትምህርት ተምረው የመቶ

እልቅና ማዕረግ አግኝተዋል::

 

በሙያቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ

በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል:: በሌሎችም ልዩ

ልዩ ሙያዎች ተሰማርተው ሠርተዋል:: በ1953

ዓ.ም. የፓርላማ አባል ሆነው ተመርጠውም

ነበር:: ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ግብርና

ልማት ዘርፍ ገቡ:: ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ

እንደገና ወደ ፓርላማ ተመለሱ::

 

በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩት አቶ

ግርማ ወልደጊዮርጊስ በ1993 ዓ.ም. የኢትዮጵያ

ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ:: ፕሬዚዳንት ሆነው

በቆዩባቸው ዓመታት በሰብዓዊ ጉዳዮች፣ በአካባቢ

ልማትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ የራሳቸውን

አሻራ ማኖር ችለዋል:: የሥልጣን ጊዜያቸውን

ከጨረሱ በኋላም ጥቂት በማይባሉ ማኅበራዊና

ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ

ይገኛሉ:: ዩኤስ ዶክተርስ ፎር አፍሪካ ሐሙስ

መስከረም 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በጌትፋም

ሆቴል ባዘጋጀው ‹‹ፕሬዚደንሺያል ላይፍ ታይም

አቺቭመንት አዋርድ›› በተሰኘው የሽልማት

ፕሮግራም ላይ ዕውቅና አግኝተዋል::

 

ከየተሻ ኤቨንትስ ኤንድ ኮሙዩኒኬሽን ጋር

በመተባበር በተዘጋጀው በዚህ የሽልማት ሥነ

ሥርዓት ላይ በሰብዓዊ ተግባር የተሰማሩ፣

ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት

የማኅበረሰቡን ችግር በመፍታት ረገድ ትልቅ

ድርሻ ያበረከቱ እንዲሁም አገሪቱን በሌላው

ዓለም እንድትታወቅ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ሚና

የተጫወቱ ተቋማት የሽልማቱ ተቋዳሽ ሆነዋል::

በእነዚህ ዘርፎች ተመርጠው ሽልማት ያገኙት

ተቋማቱ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ እንዲበቁ የጀርባ

አጥንት የሆኗቸው ሠራተኞች ሲሆኑ ከኢትዮጵያ

አየር መንገድ የማርኬቲንግና ሴልስ ዳይሬክተሯ

ወይዘሮ ሰብለወንጌል ደገፋ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ

የሴልስና ማርኬቲንግ ማኔጀሩ አቶ ኢሳያስ ሃደራ

እንዲሁም ከመቄዶኒያ የድርጅቱ መሥራች አቶ

ቢኒያም በለጠ ናቸው::

 

ከዓመታት በፊት 35 ተረጂዎችን ይዞ

የተነሳው መቄዶኒያ የመረዳጃ ማዕከል በአሁኑ

ወቅት ከ1000 በላይ ለሚሆኑ አረጋውያንና

የአዕምሮ ሕሙማን መጠጊያ ሆኗል:: የድርጅቱ

መሥራች አቶ ቢኒያም በለጠ ወደ ተቋሙ

የሚገቡ ተረጂዎች የሚንከባከባቸው ዘመድና

መጠለያ የሌላቸው ሰዎች እንደሆኑ ይናገራል::

ተቋሙ ውስን የሆነ የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ

ከመንግሥት 30 ሺሕ ካሬ ሜትር ተቀብሎ

ሕንፃ ለማስገንባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል::

ባለፈው ዓመትም ለሕንፃው ግንባታ የሚሆን

የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በማዘጋጀት መጠነኛ

ገንዘብ ማግኘት ችሏል::

 

በተመሳሳይ ዘርፎች የተሰማሩ አፍሪካውያንን

መርጦ የሚሸልመው የዩኤስ ዶክተርስ ፎር አፍሪካ

መሥራች አቶ ቴድ ዓለማየሁ እንደሚሉት፣

በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ የሽልማት ፕሮግራም

ሰዎች ና ተቋማት በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ

ለኅብረተሰቡ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ማመስገን

እንዲለመድ ያስችላል::

 

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአሜሪካ

የተቋቋመው ዩኤስ ዶክተርስ ፎር አፍሪካ በአፍሪካ

የሚከሰቱ ወረርሽኞችና ሌሎች በሽታዎች

በሕዝቡ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት

የሕክምና ባለሙያዋችን የሕክምና ግብዓቶችን

በማቅረብ ለመቀነስ ያለመ ነው:: ድርጅቱ

በአኅጉሪቱ ያለውን ሕክምና ለአፍሪካውያን

ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎንም በሕክምና ሙያ

ለተሰማሩ አፍሪካውያን የተለያዩ የአቅም ግንባታ

ሥልጠናዎች እንደሚሰጥም አቶ ቴድ ዓለማየሁ ገልፀዋል፡፡

 

ምንጭ፡- ሪፖርተር ቅፅ 22 ቁጥር 17 13

 

 

 

 

 

 

 

  

Related Topics