ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ ሮባ፣ የዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊ

‹‹ውበትን የሚመልስ ሕክምና እንሰጣለን››

 

 

 

ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ ሮባ፣ የዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ ሜዲካል ዳይሬክተር

 

ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ ሮባ የኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ በተለይ በጤናው ዘርፍ የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከሥራ ባልደረባቸው ወይዘሪት ሰብለ ነብየልዑል ጋር በመሆን አሜሪካ ያካበቱትን ዕውቀትና ሀብት ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ለማካፈል እየሠሩ ሲሆን፣ የሚያደርጓቸውን አትራፊ ያልሆኑ ሥራዎች ቀጣይና ራስን በራስ ለማገዝ ዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ ከፍተው ሰዎች በሕመም ወይም በአየር ንብረት ለውጥ ያጡትን የፊት ውበት መልሶ ለማላበስ፣ ውፍረትን ለማከም በውፍረት ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል ያለዕድሜ የሚመጣ እርጅናን በማከምና በስንፈተ ወሲብ ላይ ዘመን አመጣሽ የሕክምና ቴክኖሎጂ በጠቀም አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ዶ/ር አንተነህ የክሊኒኩ ሜዲካል ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ወይዘሪት ሰብለ ደግሞ ኦፕሬቲንግ ማናጀር ናቸው፡፡ በአገልግሎቱ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

 

ሪፖርተር፡- ስለዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ ቢያብራሩልን?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ ቁንጅናና ቁንጅናን የሚያበላሹ ከጤና እንዲሁም ከአየር ፀባይ አለመስማማት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማከም ነው፡፡ ከዕድሜ፣ ከአኗኗር፣ ከአመጋገብ ከመጠጥና ከሲጋራ ከስኳር፣ ከካንሰርና ከሌሎች ሕመሞች ጋር ተያይዞ የደከመና የተጎዳ ቆዳን ማከም ነው፡፡ አንዳንዴ ከሆርሞን መዛባት ጋር ተያይዞ ሰዎች ካለዕድሜያቸው ያረጃሉ፡፡ ሆርሞኖች በተለያየ ምክንያት ያለጊዜያቸው የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት ሲያቆሙ ፊትን ያስረጃሉ፡፡ ይህንን ሁሉ በሕክምና በማስተካከል የአንድን ሰው ጤናና ውበት ለመጠበቅ ይቻላል፡፡ ክሊኒካችንም ውበትን በመጠበቅ፣ ያለጊዜ የሚከሰት ዕርጅናን ለመከላከል ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በውፍረት ሕክምና ላይ እንሠራለን፡፡ የውፍረት ችግር ኢትዮጵያም፣ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ አለ፡፡ ዓለም አቀፍ ችግርና ወደፊትም ኢኮኖሚን የሚጎዳ መሆኑ ታውቋል፡፡ በውፍረት ምክንያትም ብዙ በሽታዎች ይመጣሉ፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ውፍረትን ለመከላከል ምን ዓይነት ሕክምና አላችሁ?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ ኢትዮጵያ ከመጣን በኋላ የውፍረት ችግር አይተናል፡፡ የአላስፈላጊ ስቦች መከማቸትና ቦርጭ የብዙዎች ችግር ሆኗል፡፡ ውፍረትን በአመጋገብና አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲሁም በሕክምና መቀነስና ማስተካከል ብሎም የወደፊት ሕይወትን ከውፍረት ጋር ተያይዘው ከሚመጡ በሽታዎች መከላከል ይቻላል፡፡ ውፍረት ሲያስቸግር፣ ለጤና ጠንቅም ሲሆን በመድኃኒት መቆጣጠር የምንችልበትን ሕክምና ክሊኒካችን ይሰጣል፡፡ ቀድመን እንዴት መከላከል እንደምንችልም ጭምር አንድ ሰው ጮማው ወይም ስቡ አንድ ቦታ ላይ ሲበዛ እንቀንሳለን ወይም እናስተካክላለን፡፡ የተጨማደደ ቦታን ያለ ቀዶ ሕክምና እናክማለን፡፡ ወደፊት ለማምጣት የምንፈልገው ደግሞ ሪጀነሬቲቭ ሜድስን ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ሪጀነሬቲቭ ሜድስን ምን ማለት ነው?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ ሴሎችን መልሶ አክሞ የተጎዳ የሰውነት ክፍልን ማከም ወይም መጠገን ማለት ነው፡፡ ሕክምናው አንዳንዴ በአንድ ጊዜ የሚያድን ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሕክምና አንድ በሽታ ከያዘ በሽታውን በመድኃኒት ማከም፣ እንዳይባባስ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ በሪጀነሬቲቭ ሜድስን ግን በቋሚ ደረጃ የማዳን ዕድል አለ፡፡ ዘርፉ አዲስ ቢሆንም፣ በሕክምናው ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ በዚህ ሕክምና ስር ስቲም ሴልና ፒአርፒ የሚባሉ የሕክምና ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ በስቲም ሴል ሕክምና የሞቱ ሴሌችን መተካት ይቻላል፡፡ የስቲም ሴል ሳይንስም የወደፊት ሕክምና ልቀት ነው፡፡ እስከዛሬ የምናደርገው ሕክምና በሽታን አያስቀለብስም፣ ይቀጥላል፡፡ ለምሳሌ ደም ብዛት ላለው ሰው ባለበት እንቆጣጠራለን እንጂ አናድንም፡፡ በስቲም ሴል ግን በሽታውን ማዳን ይቻላል፡፡ ይህ ሳይንስ ወደፊት የሚመጣ ነው፡፡ አሁን ላይ የተራቀቀ ስቲም ሴል ሕክምና ውስጥ ባንገባም የተወሰኑ ችግሮችን ለማከም እንጠቀምበታለን፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ምን ዓይነት ሕመሞችን?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ አሜሪካ ውስጥ ያለው ዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ ስንፈተ ወሲብና ስኳር በሽታን ለማከም ፈቃድ አለው፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች እንሰጣለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለውም ቅርንጫፍ፣ አሜሪካ ውስጥ የምንጠቀመውን ፕሮቶኮል አምጥተነዋል፡፡ እንደ ስቲም ሴል ሕክምና ባይራቀቅም ተመሳሳይ አሠራር የሆነውን ፒአርፒ እንተገብራለን፡፡ በዚህ ሕክምና የተጎዳ አካልን እናክማለን፡፡ ለምሳሌ ስንፈተ ወሲብን እያከምንበት ነው፡፡ ብዙዎችም ለውጥ ማምጣታቸውን ነግረውናል፡፡ ከዚህኛው በበለጠ ስቲም ሴልን ሙሉ ለሙሉ ስንተገብር ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ለስኳር በሽታ የተራቀቀ መሣሪያ ስለሚፈልግና በእኛ በኩልም ገና ዝግጅት ላይ ስለሆንን ለጊዜው ባይኖረንም፣ ወደፊት አገልግሎቱን ለመስጠት እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ መንግሥት ከተባበረን ብዙዎችን ከስኳር ሕመማቸው መታደግ እንችላለን፡፡ አሜሪካ ውስጥ የምንሰጠው የስቲም ሴል ሕክምና የስኳር ሕሙማን ሙሉ ለሙሉ ከሕመማቸው እንዲፈወሱ መድኃኒት ሳይጠቀሙ እንዲቆጣጠሩ፣ መድኃኒት እንዲቀንሱም አስችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈቀደልን ራሴም ሥልጠናውን ወስጄና ሌሎች ባለሙያዎችንም አምጥቼ ልሠራው እችላለሁ፡፡ ስንፈተ ወሲብንም ሆነ ሌሎች በሽታዎችን ለማዳን ስቲም ሴል ሕክምና አዋጭ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ በስንፈተ ወሲብ ላይ የሚደረገው የስቲም ሴል ሕክምና ከ90 በመቶ በላይ መፍትሔ ይሰጣል፡፡ ይህን ቴክኖሎጂ ወደፊት እናመጣዋለን፡፡ አሁን ላይ በመለስተኛ ቴክኖሎጂ አገልግሎቱን እየሰጠን ነው፡፡ ወደ ክሊኒካችን በብዛት የሚመጡት  የስንፈተ ወሲብ ችግር ያለባቸው ቢሆኑም፣ አጥንት፣ ፀጉር፣ ፊት ላይ ላሉ ችግሮች ሕክምናውን እንሰጣለን፡፡ ስንፈተ ወሲብን በተመለከተ የሚመጡት ወንዶች ናቸው፡፡ ሴቶች ከባህሉ ጋር ተያይዞም ሊሆን ይችላል እየመጡ አይደለም፡፡ ቫያግራ እየተጠቀሙ ስንፈተ ወሲብ ያለባቸውን ጨምሮ ሌሎችም በሰጠናቸው ሕክምና ለውጥ ማግኘታቸውን ነግረውናል፡፡ መገጣጠሚያ አካላት ላይ ያሉ ሕመሞችን ደግሞ በሕክምናው ሙሉ ለሙሉ ማዳን ይቻላል፡፡ የፀጉር መሳሳትን በማቆም ፀጉርን መልሶ ማበልፀግ ይቻላል፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ስንፈተ ወሲብ ከውስጥ ሕመም፣ ከሱስ ወይም ከስነ ልቦና ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ የምትሰጡት ሕክምና የትኛውን ያገናዘበ ነው?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ ለሕክምናው የሚመጡ ሰዎች ችግራቸው ከሳይኮሎጂ፣ ከሱስ ወይም ከውስጥ በሽታዎች ጋር መሆኑን ለማረጋገጥ የሚሞሉት መጠይቅ፣ በኋላም የሕክምና ምርመራ አለ፡፡ የሳይኮሎጂ ከሆነ ሊረዱ ወደሚችሉበት እንጠቁማለን፡፡ አንዳንዱ ከኮሌስትሮል ብዛትና ከሎሎች የውስጥ ችግሮች ጋር ተያይዞ ስንፈተ ወሲብ ያጋጥመዋል፡፡ ለምሳሌ በኮሌስትሮል የመጣ ከሆነ ኮሌስትሮሉ ወደ መደበኛ እንዲመለስ የሚያደርግ ሕክምና አለ፡፡ ከዚያ ስንፈተ ወሲቡ ይታከማል፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ የፊት ውበት፣ የመገጣጠሚያ አጥንት ሕመም፣ ስንፈተ ወሲብ፣ ያለጊዜ የመጣ እርጅናም ሆነ የስብ መከማቸት ወይም ውፍረት ላይ ለምትሰጡት አገልግሎት ቅድመ ምርመራ አለ?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ አዎ፡፡ የፊት ቆዳ ችግሮችን በሕክምና መርዳት ከመጀመራችን በፊት የተገልጋዩን የፊት ገፅ በፎቶ ወስደን ማሽን ላይ በተገጠሙ የተራቀቁ ሶፍትዌሮች እያንዳንዱ የፊት ቆዳ ያለበት ችግርና ምን ዓይነት ሕክምና እንደሚያስፈልገው እናያለን፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሕክምና የሚጀመረው፡፡ አንድ ሰው ለመክሳት ቢመጣ፣ መጀመሪያ የክብደት መቀነስ ሕክምና ከመጀመሩ በፊት ለምን ውፍረት እንደተከሰተ እንመረምራለን፡፡ ውፍረት የሚቀነሰው ለውበት ብቻ ተብሎ አይደለም፡፡ ውፍረት ከውበት ማበላሸት ባለፈም የጤና ጠንቅ ነው፡፡ እኛም በሕክምና የታገዘ የክብደት መጠን ማስተካከል አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሠለጠነው ዓለም ውፍረትን እንደ ስኳርና ደም ብዛት በሽታ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ እኛም ውፍረትን የምናየው ከበሽታ አንፃር ነው፡፡ ሰውነት ውስጥ የተከማቸ ስብ በሽታ ሲሆን፣ ጡንቻ መኖሩ ለጤና ወሳኝ ነው፡፡ ያለጥንቃቄ መክሳት የሚጎዳው ጡንቻን ስለሆነ አይመከርም፡፡ የሐኪም ምክር ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው በዳይት የከሳ መስሎት ተመልሶ ወደመደበኛ ምግቡ ሲገባ፣ ሰውነቱ በጣም የሚጨምረው፣ በዳይቱ በሰውነቱ የተከማቸውን ስብ ሳይሆን ጡንቻ ስላቃጠለ ነው፡፡ ጡንቻ የሌለው ሰው ስብን ማቃጠል አይችልም፡፡ እኛ ጋር ክብደት ለመቀነስ የሚመጣ ሰው፣ ደሙን ይመረመራል፣ የሆርሞን መዛባት ካለ እንዲስተካከል ይደረጋል፡፡ የተዛባ ሆርሞን ያለው ሰው ቀን ሙሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቢያደርግ አይከሳም፡፡ ሰዎች ውፍረት ለመቀነስ ሕክምና ከመጀመራቸው በፊት በሰውነታቸው ውስጥ፣ ምን ያህል ውኃ፣ ስብ (ጮማ)፣ አጥንት፣ ስቡ ያለው በቆዳ ውስጥ ነው ወይስ ልብ፣ ኩላሊት ወይም ጉበት ላይ የሚሉት በምርመራ ይረጋገጣሉ፡፡ በምርመራው መሠረት የሚቀንሰው እንዲቀንስ፣ የሚጨምረው እንዲጨምር ሕክምናውን እንጀምራለን፡፡ በአካላዊ ብቃት የታገዘ ዳይት እንዲጀምሩ ሲደረግም፣ ስኳር፣ ደም ብዛትና ሌሎች ችግሮች ታይተውና ታሳቢ ተደርገው ነው፡፡ የተቀናጀ ክብደትን የመቀነስ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠን ነው፡፡ በየጊዜው እየተከታተልንም ስቡ እንዲጠፋ፣ ጡንቻ እንዲጠነክር እናደርጋለን፡፡ በጣም አደገኛው ስብ በልብ፣ በጉበት እንዲሁም በኩላሊት ላይ የሚከሰተው ነው፡፡ ይህ ሰዎችን ለተለያዩ በሽታዎች ይዳርጋል፡፡ እኛ እነዚህ ከተከሰቱ የሚወገዱበት፣ ካልተከሰቱ እንዴት ጠብቆ መቆየት እንደሚቻል ሕክምናውን ከአሜሪካ ይዘን መጥተናል፡፡ የተሟሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችም አሉን፡፡ ክብደት መቀነስ በሕክምና የመታገዙ ጥቅምም ከስኳር፣ ከደም ብዛትና ከሌሎች ሕመሞች ለመታደግ ማስቻሉ ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ከምትሰጡት ሕክምና ጋር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አብሮ አለ?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ ወደፊት ምኞታችን እሱ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ችግር የራሱ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ብረት ማንሳት ውፍረትን ለመቆጣጠር ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ሴቶች አይመስላቸውም፡፡ ጡንቻን ማዳበር ውፍረትን ለመቆጣጠር፣ ጤነኛ ለመሆን፣ ወደፊት እርጅና ሲመጣ መገጣጠሚያ ላይ ችግር እንዳይፈጠር ያግዛል፡፡ እርጅና ሲመጣ ወገቤን አመመኝ፣ እግሬ አላስነሳ አለ የሚባሉት ሁሉ የሚመጡት መጀመሪያውኑ ጡንቻ ስላልጠነከረ ነው፡፡ የአካል ብቃት ሲደረግ ለማን ምን ዓይነት? ለምን ያህል ሰዓት? የሚሉት መለየት አለባቸው፡፡ ወደፊት የራሳችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ ይኖረናል፡፡ አሁን ላይ ጂም መሄድ ለማይችሉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንነግራለን፡፡ መሄድ የሚችሉት ደግሞ አሠልጣኛቸውን እንዲያገናኙን አድርገን፣ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ ማሠራት እንዳለበት/ባት እንነጋገራለን፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ውፍረታቸው ቀንሶ ቆዳቸው ለሚንዘላዘል ሰዎች የምትሰጡት ሕክምና አለ?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ አዎ፡፡ የተንዘላዘለ ቆዳ ሲኖር ሬዲዮፍሪኩዌንሲ የተባለ የተሸበሸበ ቆዳን የሚያስተካክል ሕክምና አለን፡፡ ሆኖም ከትልቅ ኪሎ ወደ ዝቅተኛ የሚገባ ሰው የሚንዘላዘለው የሰውነት ክፍሉ ከበዛ በሬዲዮፍሪኩዌንሲ ማስተካከል አይቻልም፡፡ ቀዶ ሕክምና ነው፡፡ ሆኖም ቆዳቸው በተለያየ ምክያት የተለጠጠ ሰዎች ሲከሱ የተንዘላዘለው የቆዳ ክፍል ብዙ ካልሆነ በሬዲዮፍሪኩዌንሲ እናስተካክለዋለን፡፡ ይህን ሕክምና እየሰጠን እንገኛለን፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ሰውነት ላይ የተከማቸ ስብን ያለቀዶ ሕክምና የምታስወግዱበት መሣሪያ አላችሁ? ለምሳሌ ቦርጭ፣ በሰውነት ጎንና ጎን ተርፈው የሚመጡ ስቦችን እንዴት ያለቀዶ ሕክምና ታጠፋላችሁ?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ አሜሪካ ብዙዎቹ ሰዎች የተትረፈረፈ አካላቸውን ያለቀዶ ሕክምና ማስወገድ ይመርጣሉ፡፡ ለዚህም ኩል ስክራፕቲንግ ማለትም ያለቀዶ ሕክምና ስብን የሚያስወግድ መሣሪያ አለ፡፡ በክሊኒካችንም መሣሪያውን ተጠቅመን አገልግሎቱን እየሰጠን ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ የፊት ውበት የውስጥ ጤንነት መገለጫ ሲሆን፣ ውፍረትም አስከትሎ የሚመጣቸው የጤና እክሎች አሉ፡፡ እዚህ ላይ ያለው ግንዛቤ እንዴት ነው?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ ብዙዎቹ የውስጥ ሕመሞች ፊት ላይ ይገለጻሉ፡፡ ለዚህ ነው ክሊኒካችን ውበትን ለመጠበቅና ካለዕድሜ የሚመጣ እርጅናን ለመከላከል በሕክምና የታገዘ አገልግሎት እየሰጠ ያለው፡፡ ለምሳሌ ብጉር ፊት ያበላሻል፣ ውበትን ያጠፋል፡፡ በዛው ልክ መታከም ያለበት ሕመም ነው፡፡ ብጉርን አክመን ከነበረበት መጥፎ ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጣት እንችላለን፡፡ በዚህም የተበላሸ ፊት መልሶ ውበት ይላበሳል፡፡ ውበትና ሕክምናን አጣምረን ነው የምንሠራው፡፡ በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት የፊታቸው ቆዳ የተጎዳ ሰዎችንም እናክማለን፡፡ ሙሉ ለሙሉ ማዳን የማይቻልባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ ማሻሻል ይቻላል፡፡ በበሽታ ምክንያት የሰረጎዱና ወዛቸው ጠፍቶ የተበላሹ ጉንጮችንም ማስተካከል እንችላለን፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ በውጭ ዓለም እናንተ የምትሰጧቸው የውበት ሕክምናዎች ውድ ናቸው፡፡ እዚህ ስታመጡት ዋጋው እንዴት ነው?

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ እዚህም ትንሽ ይወደዳል፡፡ ከመርፌ አንስቶ ያለን ማሽን በሙሉ ከአሜሪካ የመጣ ነው፡፡ እዛም በውድ የሚገዛ ነው፡፡ አገር ውስጥ ሲገባ ደግሞ የትራንስፖርቱ አለ፡፡ ከሁሉም በላይ 81 በመቶ ታክስ እንከፍላለን፡፡ ሥራችን ከኮስሞቲክስ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከሕክምናና ከሕክምና መድኃኒቶች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሆኖም በሜዲካል ደረጃ የምንሰጠው አገልግሎት እንደኮስሞቲክ ተቆጥሮ ከፍተኛ ግብር እንከፍላለን፡፡ በሌላ በኩል አገልግሎት እየሰጠን እንጂ ለሕክምናው የሚውሉ መድኃኒቶችን እየሸጥን አይደለንም፡፡ በአሜሪካ ቀድመን ከተማርነው የሕክምና ትምህርት በተጨማሪ ለእያንዳንዷ ተጨማሪ ትምህርት ብዙ ሺሕ ዶላር ከፍለን ሥልጠና ወስደናል፡፡

 

ወይዘሪት ሰብለ፡- አሜሪካ ቆይተን አገራችን ለመሥራት ስንመጣ፣ አገር መርዳት አለብን ባልነው ዘርፍ እየረዳን ነው፡፡ ዚኒያ ኤስቴቲክ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒኩን የከፈትነው ለትርፍ ብሎም ከሚገኘው ትርፍ ቀድመን የከፈትነውን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጀትና በትምህርት ቤት የተጀመረውን የተማሪዎች ምገባ ለማጠናከር ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም አብዛኛውን እገዛ ያደረግነው ከኪሳችን አውጥተን ነው፡፡ ከሌሎች ትንሽ እገዛ ቢኖርም በተለይ ዶ/ር አንተነህ አሜሪካ እየሠራ፣ የሠራበትን እዚህ እያወጣ ነው፡፡ ይህ ለአገራችን የምናደርገው ስጦታ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የተጎዱ ዜጎችን ማገዝ ለእኛ ትርጉም አለው፡፡ ሆኖም አንዱን በአንዱ ለመደገፍ በሚከፈቱ አገልግሎቶች ላይ ትልቅ ታክስ በተጫነ ቁጥር አገልግሎት ፈላጊው ላይ ዋጋ ይጫናል፣ በሌላ በኩል ያሰብናቸውን ለኅብረተሰቡ የሚውሉ ፕሮጀክቶች ራሳችን በራሳችን ለመደገፍ እንቸገራለን፡፡ እኔ ሥራዬን ትቼ መጥቻለሁ፡፡ በአገራችን ቀጣይነት ያለውና በሕዝቡ ላይ ለውጥ ያለው ሥራ መሥራት እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ቀደም ኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ በሚለው ድርጅታችን ሰሜን ሸዋ ዘመሮ የሚባል አካባቢ የሕክምና ጓድ ይዘን ከ300 ለማያንሱ የዓይን ሕመም ላለባቸው ሰዎች ቀዶ ሕክምና አድርገን ዓይናቸው እንዲያይ አድርገናል፡፡ የካቲት 12 ሆስፒታል የጨቅላ ሕፃናት ክፍል እንዲከፈት፣ ትልቅ ደረጃ እንዲደረስ አድርገናል፡፡ ጋንዲ ሆስፒታልም ቁሳቁስ አቅርበን የጨቅላ ሕፃናት ክፍል እንዲከፈት ረድተናል፡፡ ለየካቲት ከሰጠነው ቁሳቁስ የተረፉት ዘውዲቱ እንዲሄዱ ተደርጎ እዚህም የጨቅላ ሕፃናት ክፍል ተከፍቷል፡፡ እኛ መሠረቱ እንዲጣል ረድተን የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ክፍል አሁን ላይ በየሆስፒታሉ እየተስፋፋ ነው፡፡ የምንፈልገው እንዲህ ዓይነቱን መሠረታዊ ለውጥ ነው፡፡ በየጊዜው የሕክምና ጓድ ይዞ በመሄድ ሕክምና መስጠቱ አያዋጣም፡፡ ስለሆነም ግሪን ዴቨሎፕመንት የሚባል ፕሮፖዛል ቀርፀናል፡፡ ይህን ያደረግነው ዘመሮ ላይ በነበረን ሥራ፣ የሕዝቡን ችግር ከስር መሠረቱ መቅረፍ እንጂ ከታመመ በኋላ ማከሙ ብዙም ዋጋ እንደሌለው በመረዳታችን ነው፡፡ ባየነው መሠረት ሰው ከኑሮው አኳያ ለሕመም እየተጋለጠ ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ካለማግኘት፣ ከግልና ከአካባቢ ንጽሕና ጉድለት፣ ከንጹህ ውኃ አቅርቦት እጥረት ጋር የተያያዘ ችግር አለ፡፡ ከውፍረት ጋር የተያያዘ በሽታ አላየንባቸውም፡፡ ስለሆነም መሠረታዊ የጤና አጠባበቅ ላይ ከሠራን ማኅበረሰቡን መታደግ እንችላለን፡፡ መሠረተ ልማቱን ከረዳን፣ ራሳቸውን እንዲመግቡ፣ ሥራ እንዲፈጠር ካደረግን ኑሯቸው ይስተካከላል፡፡ በዛው ልክ ጤናቸው ይጠበቃል፡፡ ይህንን  ፕሮፖዛል ለመተግበር ከሚሊዮን ዶላር በላይ እንፈልጋለን፡፡ አንዱ ምንጫችን ደግሞ የከፈትነው ክሊኒክ ነው፡፡ ዓላማችንም ክሊኒኩ እንዳሰብነው መሥራት ከቻለ ብዙ ገንዘብ አመንጭተን ሌሎች ፕሮጀክቶችን መደገፍ ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡‑ ክሊኒኩ እንደ ሜዲካል ቱሪዝም ሊያገለግል የሚችል ነው፡፡ እዚህ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?

 

ወይዘሪት ሰብለ፡- እንዳሰብነው መሄድ ከቻልን ክሊኒኩ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ሊያመጣ ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ የምንሰጣቸው አገልግሎቶች በአፍሪካ የሉም፡፡ አንዳንዶቹ አሉ፡፡ አየር መንገዳችን ባለው ሽፋን ብዙዎችን መድረስ ከቻልን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ብቻ ሳይሆን ከውጭ ያሉ ሰዎችንም አምጥተን ማከም እንችላለን፡፡ ሜዲካል ቱሪዝሙን አስፋፍተን አገራችንንና ራሳችንን መጥቀም እንችላለን፡፡

 

ዶ/ር አንተነህ፡‑ በዓለም የኤስቴቲክ ገበያው ተፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኤስቴቲክ ወይም ውበት ላይ ብትሠራና አገልግሎቱን ብታስፋፋ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተሻለ ተገልጋይ ልትስብ ትችላለች፡፡ ለምሳሌ የፀጉር መልሶ ማብቀል ላይ ብንሠራ ቀላል ነው፡፡ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ማምጣትም እንችላለን፡፡ ስቲም ሴል ላይ ብንሠራ መካከለኛው ምሥራቅን መያዝ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም መካከለኛው ምሥራቅ ላይ ውፍረት ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎችም አሉ፡፡ አገልግሎቱን በመስጠታችን የምናገኘው የውጭ ምንዛሪ ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቷን የአገልግሎቱ መዳረሻ መሆኗን ከሚገልጽ ካርታ ላይ እንድትሰፍር እናደርጋለን፡፡ ዓላማችንም ይኸው ነው፡፡

ምንጭ፡- ሜዲካል መጽሄት