ስለ ሲጋራ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ስለ ሲጋራ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

 

Image result for cigarette smoker sad

 

ከእነዚህ ነጥቦች መካከል የአንተን ስሜት በሚገልጸው ላይ ✔ አድርግ።

□የማወቅ ጉጉት አለኝ

 

□ ውጥረት በዝቶብኛል

 

□ ተቀባይነት ማግኘት እፈልጋለሁ

 

□ ክብደት መቀነስ እፈልጋለሁ

 

ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች ቢያንስ በአንዱ ላይ ምልክት አድርገሃል? ከሆነ ሲጋራ የሚያጨሱ ወይም ለማጨስ የሚያስቡ እኩዮችህም እንደ አንተ ይሰማቸዋል።* እነዚህ ወጣቶች ከተናገሩት ሐሳብ አንዳንዶቹን እንደ ምሳሌ እንመልከት፦

 

የማወቅ ጉጉት። “ማጨስ ምን ስሜት እንደሚፈጥር ማወቅ ስለፈለግሁ በትምህርት ቤት ከአንዲት ልጅ ሲጋራ ተቀብዬ በድብቅ አጨስኩ።”—ትሬሲ

 

ውጥረትን መቋቋምና ተቀባይነት ማግኘት። “በትምህርት ቤት ያሉ ልጆች ውጥረት ሲበዛባቸው ‘ሲጋራ ባገኘሁ’ ይላሉ፤ ከዚያም ካጨሱ በኋላ ‘አሁን ቀለል አለኝ!’ በማለት ይናገራሉ። እኔም ውጥረት ሲያጋጥመኝ እንዲህ ማድረግ ያምረኛል።”—ኒኪ

 

ክብደት መቀነስ። “አንዳንድ ሴቶች የሚያጨሱት ላለመወፈር ስለሚፈልጉ ነው፤ ይህ ዘዴ ምግብ ለመቀነስ ከመሞከር ይበልጥ ቀላል ነው!”—ሳማንታ

 

አንተም ማጨስ ለመጀመር እያሰብህ ይሆናል፤ አሊያም ስታጨስ ቆይተህ ሊሆን ይችላል፤ ያም ሆነ ይህ ሲጋራ ከመለኮስህ በፊት ቆም ብለህ አስብ። መንጠቆ ላይ የተንጠለጠለን ምግብ ለመብላት እንደሚቸኩል ዓሣ አትሁን። ዓሣው ምግቡን መቅመስ ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ሕይወቱን ስለሚያጣ አተርፍ ባይ አጉዳይ መሆኑ አይቀርም! ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል ‘በትክክል ማሰብህ’ የተሻለ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:1) እስቲ ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ስጥ።

 

ስለ ሲጋራ ምን ያህል ታውቃለህ?

 

እውነት ወይም ሐሰት በል።

 

ሀ. ማጨስ ውጥረትን ይቀንሳል።

 

□ እውነት □ ሐሰት

ለ. የሲጋራውን ጭስ እንዳለ አወጣዋለሁ።

 

□ እውነት □ ሐሰት

ሐ. ወጣት ስለሆንኩ ማጨስ ጤንነቴን አይጎዳውም።

 

□ እውነት □ ሐሰት

መ. ባጨስ ተቃራኒ ፆታን መማረክ እችላለሁ።

 

□ እውነት □ ሐሰት

ሠ. ባጨስ የምጎዳው ራሴን ብቻ ነው።

 

□ እውነት □ ሐሰት

ረ. የእኔ ማጨስ አለማጨስ አምላክን ያን ያህል አያሳስበውም።

 

□ እውነት □ ሐሰት

መልስ

 

ሀ. ሐሰት። ማጨስ የውጥረት ስሜትን በተወሰነ መጠን ቢቀንስም በሲጋራ ውስጥ ያለው ኒኮቲን በውጥረት ጊዜ ሰውነታችን የሚያመነጫቸውን ሆርሞኖች መጠን ከፍ እንደሚያደርገው የሳይንስ ሊቃውንት ደርሰውበታል።

 

ለ. ሐሰት። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ወደ ውስጥ በምትስበው የሲጋራ ጭስ ውስጥ ከሚገኙት ንጥረ ነገሮች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሰውነትህ ውስጥ ይቀራሉ።

 

ሐ. ሐሰት። ማጨስ በጤንነትህ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ብዙ ባጨስክ መጠን እየጨመረ የሚሄድ ቢሆንም አንዳንዶቹ ጉዳቶች ማጨስ ከጀመርክ ብዙም ሳይቆይ መታየት ሊጀምሩ ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች ሱስ የሚይዛቸው የመጀመሪያውን ሲጋራ እንዳጨሱ ነው። ሳንባህ አየር የመያዝ አቅሙ የሚቀንስ ሲሆን የማይለቅ ሳል ሊያስቸግርህ ይችላል። እንዲሁም ያለ ዕድሜህ ቆዳህ ይሸበሸባል። በተጨማሪም ማጨስ ለስንፈተ ወሲብ ሊያጋልጥህ እንዲሁም ድንገተኛ የሆነ የመሸበር ስሜትና የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትልብህ ይችላል።

 

መ. ሐሰት። ሎይድ ጆንስተን የተባሉ ተመራማሪ እንደገለጹት አብዛኞቹ ወጣቶች፣ ሲጋራ የሚያጨሱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ተቃራኒ ፆታ ያላቸው ልጆች “ያን ያህል አይማርኳቸውም።”

 

ሠ. ሐሰት። በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ የማያጨሱ ሰዎች ለሲጋራ ጭስ በመጋለጣቸው ብቻ ለሞት ይዳረጋሉ፤ የአንተ ማጨስ ቤተሰቦችህን፣ ጓደኞችህን አልፎ ተርፎም የቤት እንስሳትህን ይጎዳል።

 

ረ. ሐሰት። አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች “ሥጋን . . . ከሚያረክስ ነገር ሁሉ” ራሳቸውን ማንጻት አለባቸው። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ማጨስ ሰውነትን እንደሚያረክስ ምንም ጥርጥር የለውም። ሲጋራ በማጨስ ሰውነትህን የምታረክስ እንዲሁም የራስህንም ሆነ የሌሎችን ጤንነት የምትጎዳ ከሆነ የአምላክ ወዳጅ መሆን አትችልም።—

 

ተጽዕኖውን መቋቋም

 

ታዲያ አንድ ልጅ እንድታጨስ ቢጋብዝህ ምን ታደርጋለህ? ብዙውን ጊዜ “ይቅርብኝ፣ አላጨስም” የሚል አጭር ሆኖም ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት ይበቃል። ልጁ መጎትጎቱን ቢቀጥል አልፎ ተርፎም ቢያሾፍብህ እንኳ ላለማጨስ የመምረጥ መብት እንዳለህ አስታውስ። እንዲህ ልትለው ትችላለህ፦

 

● “ሲጋራ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ስለማውቅ ላለማጨስ ወስኛለሁ።”

 

● “ወደፊት ልደርስባቸው ያሰብኳቸው ግቦች ስላሉኝ ሳንባዬን እፈልገዋለሁ።”

 

● “የራሴን ምርጫ የማድረግ መብት የለኝም?”

 

ይሁንና በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች ሁሉ አንተም ከሁሉ በላይ የሚከብድህ የራስህን ምኞት ማሸነፍ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ከታች በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰልህ ይህን ስሜት ለማሸነፍ ይረዳሃል፦

 

● ማጨሴ የሚያስገኝልኝ ጥቅም አለ? ለምሳሌ ያህል፣ በእኩዮቼ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስል ማጨስ ብጀምር ሌላ የሚያመሳስለን ነገር እስከሌለ ድረስ ስላጨስኩ ብቻ ጓደኛቸው ያደርጉኛል? ደግሞስ ጤንነቴ ቢጎዳ ደንታ የማይሰጣቸው ልጆች ጓደኝነት ምን ይጠቅመኛል?

 

● ማጨስ ምን ያህል ወጪ ያስወጣኛል? ጤንነቴንና ሌሎች ለእኔ ያላቸውን ግምትስ የሚነካው እንዴት ነው?

 

● ለሲጋራ ብዬ ከአምላክ ጋር ያለኝን ወዳጅነት ማበላሸት ያዋጣኛል?

 

ይሁንና በሲጋራ ሱስ ተጠምደህ ከሆነስ? ከሱስህ ለመላቀቅ ምን ማድረግ ትችላለህ?

 

ማቆም የሚቻልበት መንገድ

 

1. ራስህን አሳምን። ለማቆም ያነሳሱህን ምክንያቶች ጻፍ፤ ከዚያም እነዚህን ምክንያቶች በየጊዜው መለስ እያልክ ተመልከታቸው። በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆነህ ለመገኘት ያለህ ፍላጎት ሱሱን ለማሸነፍ የሚያስችል ኃይል ይሰጥሃል።—ሮም 12:1፤ ኤፌሶን 4:17-19

 

2. እርዳታ ለማግኘት ሞክር። በድብቅ ታጨስ ከነበረ ሁኔታውን ለሌሎች ተናግረህ እንዲረዱህ ጠይቅ። ማጨስህን ደብቀሃቸው ለነበሩት ሰዎች አሁን ለማቆም እንዳሰብክና የእነሱን ድጋፍ እንደምትፈልግ ንገራቸው። አምላክን ለማገልገል የምትፈልግ ከሆነ እሱ እንዲረዳህ ጸልይ።—1 ዮሐንስ 5:14

 

3. የምታቆምበትን ቀን ወስን። ለዝግጅት የሚሆን ሁለት ሳምንት ወይም ከዚያ ያነሰ ጊዜ መድብና ለማቆም የወሰንክበትን ዕለት በቀን መቁጠሪያህ ላይ ምልክት አድርግበት። በዚያ ቀን እንደምታቆም ለቤተሰቦችህና ለጓደኞችህ ንገራቸው።

 

4. በደንብ ፈትሽ፤ ምንም ሳታስቀር አስወግድ። ለማቆም የወሰንክበት ቀን ከመድረሱ በፊት ክፍልህን፣ መኪናህንና ልብስህን በደንብ ፈትሽ። ሲጋራ ካገኘህ ጣለው። ላይተሮችን፣ ክብሪቶችንና መኮስተሪያዎችን አስወግድ።

 

5. ማጨስ በማቆምህ የሚኖርህን የሕመም ወይም ሌላ ዓይነት ስሜት ለመቋቋም የሚረዱህ መንገዶች ፈልግ። የፍራፍሬ ጭማቂ ወይም ውኃ በብዛት ጠጣ፤ እንዲሁም ለእንቅልፍ ተጨማሪ ጊዜ መድብ። በማቆምህ ምክንያት የሚፈጠርብህ መጥፎ ስሜት ጊዜያዊ መሆኑን፣ የምታገኛቸው ጥቅሞች ግን ዘላቂ መሆናቸውን አስታውስ!

 

6. እንዲያገረሽብህ ከሚያደርጉ ነገሮች ራቅ። አጭስ አጭስ የሚል ስሜት ከሚፈጥሩብህ ቦታዎችና ሁኔታዎች ራቅ። በተጨማሪም ከሚያጨሱ ሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት ማቋረጥ ሊያስፈልግህ ይችላል።

 

አትታለል

 

የትንባሆ ኩባንያዎች ለማስታወቂያ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣሉ። እነዚህ ማስታወቂያዎች ይበልጥ የሚያነጣጥሩት በማን ላይ ነው? አንድ የትንባሆ ፋብሪካ የውስጥ ሰነድ “የዛሬዎቹ ወጣቶች የነገ ቋሚ ደንበኞቻችን ናቸው” ይላል።

 

የትንባሆ ኩባንያዎች ኪስህን እንዲያራቁቱት አትፍቀድ። በማባበያቸው ተማርከህ በወጥመዳቸው እንዳትያዝ ተጠንቀቅ። እነሱም ሆኑ የሚያጨሱ እኩዮችህ እንድታጨስ የሚገፋፉህ ለአንተ አስበው አይደለም። እነሱን ከመስማት ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር በማዳመጥ ለአንተ “የሚበጅህ” ምን እንደሆነ እወቅ።

ምንጭ፡- የወጣቶች ጥያቄ