ኮንሶ ከአዲስ አበባ በ595 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ወረዳ ስትሆን

የኮንሶ ተፈጥሮዎች

 

Image result for የኮንሶ ባህል

 

ኮንሶ ከአዲስ አበባ በ595 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ወረዳ ስትሆን ካራት የተባለች የወረዳዋ መዲና ላይ ቱሪስቶች መዳረሻቸውን ያደርጋሉ። በወረዳው ዘጠኝ ያህል ጐሳዎች የሚገኙ ሲሆን “አፋኾንሶ” የተባለ ከኦሮምኛ ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው ቋንቋ ይናገራሉ። እጅግ ማራኪ ትህትና ያለው የኮንሶ ማህበረሰብ፤ በስራ ታታሪነቱ የሚታወቅ ሲሆን በሸለቆና በተራራ የተከበበውን አስቸጋሪ መልክአ ምድር በአገር በቀል እውቀቱ በእርከን ስራ አፈሩን ከመሸርሸር አድኖ፣ ተራራማውን መሬትም አስውቦ በስፋት በእርሻ ስራ የሚተዳደር ማህበረሰብ ነው፡፡ የኮንሶ ህዝብ የራሱ ባህል፣ የዳኝነት ስርዓት፣ አለባበስ እና ጭፈራ ያለው ሲሆን በተለይም የተፈጥሮ መልክአ ምድሩ በ2003 ዓ.ም በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ ቱሪስቶችን የመሳብ ጅምር እየታየና ከዘርፉም በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

ይሁን እንጂ የኢንተርኔት፣ የመብራትና የውሃ ችግር የኮንሶ ህዝብ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ከቡልጋሪያ የመጣችው ቱሪስት ማሪያና አዶልፍ፤ ፍላጐቶቼ አልተሟሉም ያለችው ያለ ምክንያት አይደለም። የኮንሶ መዲና ካራት ገና በማደግ ላይ ያለች ከትንንሽ ከተሞች የምትመደበ ከተማ ናት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ስድስት ሆቴሎችና ሁለት ሎጆች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ያም ሆኖ በአስደናቂ ተፈጥሮ የተከበበችው የኮንሶ ወረዳ፤ በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ልዩ ተፈጥሮዎች አሏት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከ300 ዓመት በፊት በንፋስ ተሸርሽሮ የተለያዩ የህንፃ ቅርፆችን ይዞ የቀረውና “ኒውዮርክ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ቦታ አንዱ ሲሆን ከካራት ከተማ በ17 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አፈር እንዳይሸረሸር በዘየዱት መላ ተፈጥሮን ምቹ ያደረጉበት የእርከን ስራቸው ሲሆን ሶስተኛው ባህላዊ ከተሞቻቸው (አምባ መንደሮቻቸው) በዓለም ቅርሰነት ተመዝግበዋል። ለዚህም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህል፣ የትምህርትና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) በካራት ከተማ እምብርት ላይ “ኮንሶ የአለም ቅርስ መገኛ” የሚል ሀውልት ያቆመው፡፡ የኮንሶ ወረዳም ይህንኑ በማስመልከት ቅርሶቹ የተመዘገቡበት ሰኔ ወር መዳረሻ ላይ በየአመቱ የባህል ፌስቲቫል ያዘጋጃል፡፡ ዘንድሮም ከግንቦት 23 እስከ 26 ቀን 2006 ዓ.ም የቆዬ የባህል ፌስቲቫል በካራት ከተማ የተካሄደ ሲሆን፤ ዘጠኙም ጐሳዎች የተገኙበት የጐዳና ላይ ትዕይንት፣ የካራት ዲስትሪክት ሆስፒታል ምረቃ፣ የስድስት ጤና ጣቢያዎች ምረቃ፣ የከተማ አስተዳደሩ እና ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ለመገንባት ሁለት የመሰረት ድንጋዮች የማስቀመጥ ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡ ለኮንሶ ህፃናት ግንዛቤ የሚውል “ኮንሶን ለህፃናት” የተሰኘ የቱሪዝም መጽሐፍና “ሴራኦታ ኮንሶ” የተባለ የኮንሶ ብሔረሰብ የባህል ህግ ስርዓትን የሚያስቃኝ መጽሐፍ ምረቃም የዘንድሮው ፌስቲቫል አካላት ነበሩ፡፡

 

በበዓሉ ለመታደም ወደ ኮንሶ ከተጓዙት ጋዜጠኞች አንዷ ነኝ፡፡ ኮንሶ ስሄድ የመጀመሪያዬ ነው። የህዝቡ አቀባበል፣ ትህትናው በጣም ይማርካል፡፡ ካራት ከተማ እንግዶቿን ለመቀበል አደባባዩ ላይ ዳስ ጥላ ትጠብቃለች። ሁሉም ደስ ይላል፡፡ እኔ ከተማዋን ወድጃታለሁ ደግሞ የሚጐድላት አለ፤ ለዚህች ከተማ ልቀኝላትም ዳዳኝ፡፡ ኔትዎርክ የለም እንጂ ኔትዎርክ ቢኖር ከትሞ መቀመጥ ኮንሶ ላይ ነበር… አልኩኝ ለራሴ፡፡

 

 

ኒዮርክን ለመጐብኘት በሄድንበት ጊዜ አይን አፍዝዝ፣ ተፈጥሮው በግርምት አፍን እጅ ላይ ያስከድናል። በድፍረት ገደሉን ወርደን እስከ ዋናው ኒውዮርክን መሳይ የአፈር ህንፃ የሰራው ዋሻ ድረስ ሄድኩኝ፡፡

 

እጄን ይዞ ገደሉን ያወረደኝ የግብርና ባለሙያ የሆነው የኮንሶ ወጣት፤ “ሚኪያ በሀይሉ ‹ደለለኝ› የሚለውን ዘፈን እዚህ ቦታ ላይ ነበር የዘፈነችው፤ ስትሞት እዚህ ቦታ ላይ ተሰብስበን አለቀስን” በማለት የዘፈኑ ክሊፕ የተሰራበትን ቦታ በእጅ ጠቆመኝ፡፡ ጐብኝተን ስንጨርስ ያንን ያገጠጠ ገደል ወጥተን ጫፍ ላይ ስንደርስ፣ ድካሙ ውሃ ውሃ ቢያሰኘንም ጫፉ ላይ የሚላስ የሚቀመስ አልነበረም። ለምን ብለን ስንጠይቅ ከአስጐብኚዎቻችን አንዱ “እዚህ በታ ላይ የምታያቸውን ሁለት ጐጆዎች፣ ከተማ አስተዳደሩ የሰራቸው ለጐብኚዎች ማረፊያ እንዲሆኑና ሻይ ቡና፣ ለስላሳና ውሃዎች እንዲሸጡበት ታስቦ ቢሆንም ለምን እንደተረሱ አላውቅም አለኝ”። በቃ ቱሪዝም አልገባንም ማለት ነው? ብዬ ራሴን ጠየቅሁኝ፡፡ ከኒዮርክ ስንመለስ ዩኔስኮ በለም ቅርስነት የመዘገባቸውን ባህላዊ ከተሞች በኮንሶዎች አጠራር (ፓሌታዎችን) ጐበኘን፡፡ አይን አፍዝዙ ባህላዊ መንደር እንዴት ተመሠረተ? የካቡ አጥር እንዴት ረዘመ? የካቡ ክብነት ከምን የመጣ ነው? የሚለውና መሰል በአምባ መንደሮቹ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ትሩፋቶች በግርምት አቅልን ያስታሉ፡፡ እስቲ ከመንደሮቹ አንዱ የሆነውን የጋሞሌን ባህላዊ መንደር ላስቃኛችሁ፡፡

 

የጋሞሌ ባህላዊ ከተማ (ፓሌታ)

አቶ ገረሱ ካውሶ ቀደም ሲል የኮንሶ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ የሁለተኛ አመት ተማሪ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ገረሱ ገለፃ፤ አምባ መንደሮቹ እረጅም እድሜ ያላቸው ሲሆኑ ከ800 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ አምባ መንደሮቹ ከ35 በላይ ቢሆኑም ዩኔስኮ በናሙናነት በአለም ቅርስነት የመዘገባቸው 12ቱን ነው። ከእነዚህም መንደሮች አንዱ “ጋሞሌ” የተባለው ባህላዊ ከተማ (ፓሌታ) ሲሆን ይህ መንደር ዘጠኝ ዙር ክብ የካብ አጥሮች አሉት፡፡ የካብ አጥሮቹም በጣም ከፍታ ያላቸው ሲሆኑ ከሌላው ከተማ ጐላ ብሎም ይታያል። “ቀደምት የፓሌታዎቹ መስራች አያቶች ከብዙ ነገር ጋር ትግል ነበረባቸው፡፡ እርስ በእርሳቸው ይጋጩ ነበር፡፡ ከዱር አውሬዎችም ጋር ይታገሉ ነበር፡፡ አነዚህን ነገሮች ለመከላከል ተሰብስበው መንደር ለመመስረትና ትልልቅ የድንጋይ ካብ አጥሮችን ለመካብ ተገደዋል” ይላሉ አቶ ገረሱ ካውሶ፡፡ እንደ ባለሙያው ገለፃ፤ ክብ ክብ የካብ አጥሮቹ ዘጠኝ ዙር ሲሆኑ ዘጠኝ ትውልድን ይወክላሉ፡፡

 

የመጀመሪያዎቹ መስራቾች መሃል ላይ ቤታቸውን ሰርተው ዙሪያውን በትልቅ የድንጋይ ካብ ሲያጥሩ፣ ከእነሱ የሚወለዱት ራሳቸውን ችለው ከዚያ ክብ ይወጡና የራሳቸውን ሌላ ክብ መንደር ይፈጥራሉ፡፡ የልጅ ልጆችም እንዲሁ፡፡

የጋሞሌ መንደርም ዘጠኝ ክብ አጥሮች ያሉት ሲሆን ዘጠኝ የልጅ ልጅ ልጅ ሀረጐች እንዳሉት ያሳያል፡፡ በፓሌታዎቹ ውስጥ ሞራዎች፣ ኦላሂታ፣ ካዎ እና መሰል ባህላዊ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ መንደሮች ጉብኝት ሲያደርጉ ድንገት ሳት ብሎዎት አንዱ መንገድ ውስጥ ከገቡ ተመልሰው ለመውጣት ማጣፊያው ያጥረዎታል። አብረው ለጉብኝት ከሄዱት ጓደኞችዎ ጋር ተመልሰው ለመገናኘት የሰዓታት ፍለጋ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

 

የፓሌታዎቹ ሞራዎች

የኮንሶ ማህበረሰብ ጥብቅ የሆነ የአስተዳደር ስርዓት ያለው ሲሆን ከላይ እስከታችም የራሱ መስመር ያለው ሲሆን ይህን ልምድና ወጉን የሚካፈልበት፣ ራሱን የቻለ ማዕከል ያለው ነው፡፡ ይህ ማዕከል ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዳለው የስነ - ማህበረሰብ ባለሙያው አቶ ገረሱ ይናገራሉ፡፡ አደባባዩ “ሞራ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የማህበረሰብ መሰብሰቢያ አደባባይ ነው፡፡ በዚህ ሞራ ላይ አዋጅ ይነገራል፣ እርቅ ይከናወናል፣ ውይይቶችና የተለያዩ ስምምነቶች ይደረጋሉ፡፡ ከጐሳ መሪዎች የሚወጡ መልዕክቶች ለህብረተሰቡም ይተላለፉበታል። ሞራ ከዚህም ባለፈ ህፃናትና ወጣቶች ከትልልቅ አባቶች የህይወት ልምድ የሚካፈሉበት ቦታ ሲሆን የህይወት ክህሎትም የሚማሩበት እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ “በሞራዎቹ ዙሪያ አባቶች ተሰብስበው ለመንደሩ ህፃናት ተረት ያወራሉ፣ እኔ ሞራ ላይ ተረት ተምሬያለሁ፣ አባቶች ክራር ይዘው የህፃናት ጭፈራ ይለማመዳሉ” ያሉት ባለሙያው፤ ህፃናት ሲጨፍሩ ጭፈራውን የሚገመግም አካል፣ ሞራ ላይ ተቀምጦ “ይሄ ትክክል ነው፤ አይደለም” በሚል አስተያየት እንደሚሰጥና የባህላዊ አይዶል ሾው አይነት ባህሪ እንዳለው በጉብኝቴ ወቅት አቶ ገረሱ አጫውተውኛል፡፡ በሞራው (በአደባባዩ) መሀል ላይ የመኝታ ቆጥ ያለው ትልቅ ሳር ቤት የሚገኝ ሲሆን በመኝታው ላይ የመንደሩ ወጣቶችና አልፎ አልፎ አባቶችም ተቀላቅለው ያድሩበታል፡፡

 

የማደሪያ ሳር ቤቱ ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው፤ እንደ ባለሙያው ገለፃ፡፡ አንደኛ ወጣቶቹ ተሰብስበው ሲያድሩ በመንደሩ የእሳት አደጋ ቢነሳ፣ አውሬ መንደር ውስጥ ገብቶ ጉዳት ሊያደርስ ቢሞክር፣ ባልና ሚስት ተጣልተው ጩኸት ቢነሳ፣ ከተሰበሱበበት ወጥተው ለተከሰተው ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ያመቻቸዋል። ሁለተኛው ምክንያት የኮንሶ ህዝብ የመከላከያ የካብ አጥሮቹን የሚሰራው ትልልቅ ድንጋዮችን በሸክም ከሩቅ ቦታ እያመጠ በመሆኑ፣ በየቀኑ ከሚስቱ ጋር እያደረ የግብረ ስጋ ግንኙነት በማድረግ፣ ጉልበቱን እንዳያደክም ይረዳዋል፡፡ ሶስተኛውና አስገራሚው ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ባልነበረበት ጊዜ ሚስት ቶሎ ቶሎ እየወለደች የቤተሰቡ ቁጥር በዝቶ ችግር ላይ እንዳይወድቁ፣ እንደ ቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ይጠቀሙበት ነበር - የወጣቶቹን በሞራው ሳር ቤት ውስጥ ማደር፡፡ በሌላ በኩል ሌሊት ወጣቶቹ ከአባቶች ጋር ሲያድሩ በርካታ ጉዳዮችን እያነሱ እንዲወያዩ ይረዳቸዋል፡፡

 

የሞራ አይነቶች

የኮንሶ ማህበረሰብ አደባባዮች (ሞራዎች) ሶስት አይነት ናቸው፡፡ አንደኛው ቀለል ያለ ሆኖ በየንኡስ መንደሮቹ የሚገኝ ሲሆን ሰዎች በየቀኑ ተሰብስበው ይጨዋወታሉ፤ ጨቃ የተባለውን ባህላዊ መጠጥ ይጠጣሉ፡፡ ከስራ በኋላ አየር ለመቀበል በሞራው ዙሪያ ተሰባስበው ገበጣ የተባለውን ባህላዊ ጨዋታ ይጫወታሉ። በጉብኝቴም ወቅት ይህንኑ አስተውያለሁ። ሁለተኛው የሞራ አይነት የእምነት አገልግሎት የሚሰጥበት ሲሆን የተጣሉ ሰዎች የሚማማሉበት ነው፡፡

 

በአካባቢው ከብት ሲጠፋ፣ ሰው ሞቶ ሲገኝና ሌላ ንብረት ሲጠፋ፣ የገደለው ወይም የሰረቀው ሰው ተሰውሮ ካደረገው የተጠረጠረው ሰው ወደ ሞራው ይቀርባል፡፡ በሞራው ውስጥ የመሀላ ድንጋዮች የሚገኙ ሲሆን የተጠረጠረው ሰው “ይህን በደል ፈጽሜ ከሆነ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ” ሲል መሀላ ይፈጽማል። በማህበረሰቡ አንድ ሰው በውሸት ሞራ ላይ ቀርቦ ድንጋዮቹን ነክቶ ከማለ በደቂቃዎች ውስጥ ይቀሰፋል ተብሎ ስለሚታመን ማንም ሰው በውሸት እንደማይምል አቶ ገረሱ ይናገራሉ፡፡ ይህ ሞራ በተጨማሪም በአዝመራ ወቅት ዝናብ ሲጠፋና የተዘራ ሰብል ሲደርቅ፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ተሰብስበው ፈጣሪያቸውን ዝናብ እንዲያዘንብና ከድርቅ እንዲያድናቸው የሚለማመኑበት የፀሎት ስፍራም ነው፡፡

 

ሶስተኛው አይነት ሞራ ትልልቅ አመታዊ በዓላት ሲከበሩ ብቻ የሚያገለግል ሲሆን ከበዓላቱ አንዱ የትውልድ የስልጣን ርክክብ በዓል ነው። በ18 ዓመት አንዴ የሚከናወነውና በማህበረሰቡ “ኸልዳ” ተብሎ የሚጠራው በዓል 18 አመት ማህበረሰቡን ሲያገለግል ከቆየ በኋላ ስልጣኑን ለሌላ አዲስ ትውልድ በሚያስረክብበት ጊዜ በዚህ ሞራ ውስጥ ይካሄዳል። 18 አመት ስልጣን ይዞ ህዝቡን ሲመራ የነበረው ትውልድ፤ ለአዲሱ ሲያስረክብ “እኛ ይህንን ሰርተናል እናንተ የተሻለ ስሩ፣ ተባረኩ” ብሎ በሰላማዊ መንገድ ስልጣኑን ያስረክባል። መራቂ ሽማግሌም በትልቅ ጐድጓዳ እቃ ወተት ከያዘ በኋላ፣ በአበባ ወተቱን ነክሮ እየረጨ ቡራኬ ይሰጣል፡፡ አደራም ይጥላል፡፡ ይህ የስልጣን ርክክብ የሚካሄድበትና ሌላ በዓላት ሲኖሩ ብቻ የሚከፈት አደባባይ (ሞራ) ነው፡፡

 

“ኦላሂታ”

በኮንሶ ህዝቦች “ኦላሂታ” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን የትውልድ የስልጣን ፖል ነው፡፡ 18 ዓመት ካገለገለው ትውልድ አዲስ ስልጣን የሚረከበው ትውልድ ስልጣን ሲረከብ የራሱን የትውልድ ፖል (ኦላሂታ) ሞራው በሚገኝበት አደባባይ ይተከላል፡፡ ይህ የትውልዱ ማስታወሻ ነው፡፡

 

ለኦላሂታ የሚያገለግለው እንጨት ፅድ ሲሆን ከየትኛውም ቦታ በዘፈቀደ የሚቆረጥ እንዳልሆነ አቶ ገረሱ ይናገራሉ፡፡ ዛፉ በጐሳ መሪዎች መኖሪያ አካባቢ በጥብቅ ደንነት የሚጠበቅ ሲሆን ምስጥ የማይበላውና የማይበሰብስ መሆኑ ተረጋግጦና በጐሳ መሪዎች ተባርኮ እንደሚቆረጥም ይነገራል። ስልጣኑን ሲረከብ ይህን ፖል (ኦላሂታ) የተከለው ትውልድ 18 አመት ካገለገለ በኋላ ስልጣኑን ሲያስረክብ  መጪው አዲስ ትውልድ ስልጣን ሲይዝ የመጀመሪያው አስረካቢ ፖል የተከለበት ጐን አዲስ ኦላሂታ ተክሎ ስልጣኑን ይረከባል፡፡ በጉብኝቴ ወቅት የተለያዩ ትውልዶች ስልጣን ሲይዙ የተከሏቸው ፖሎች እጅብ ብለው ቆመው ባንዲራ ተሰቅሎባቸው ተመልክቻለሁ፡፡

 

“ዋካዎች”

በኮንሶ ማህበረሰብ ዋካዎች የሚባሉት በአካባቢው ጀብድ ለሠራ፣ በጦርነት ድል ለነሳ፣ አንበሳና ነብር ለገደለ በአጠቃላይ በማህበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቶ ላለፈ ሰው የሚተከሉ ሶስት ትክል ረጃጅም ድንጋዮች ሲሆኑ እነዚህ ድንጋዮች ለጀብደኛው እንደ ሀውልት ሆነው በሞራው ፊት ለፊት ከኦላሂታዎቹ (ፖሎቹ) ጐን ይገኛሉ። በነገራችን ላይ ካራት ከተማ ውስጥ ከዋናው አደባባይ አለፍ ብሎ አውላላ ሜዳ ላይ የተተከሉ ሶስት ድንጋዮች አይቻለሁ፡፡

 

በእለቱ በከተማዋ የሚውለውን የሰኞ ገበያ ለመጐብኘት ስንሄድ ነው ዋካዎቹን የተመለከትኳቸው። አንዱን የአካባቢውን ተወላጅ፣ ስለ ዋካዎቹና ለማን እንደተተከሉ ስጠይቀው፤ “ለጓድ መለሴ የተተከሉ ዋካዎች ናቸው” ሲል ምላሽ ሰጠኝ፡፡ የኮንሶ ማህበረሰብ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን “ጓድ መለሴ” ብሎ ነው የሚጠራቸው፡፡ በተለያዩ ንግግሮች እና መዝሙሮች ውስጥ በአፋኾንሶ “ጓድ መለሴ” የሚል ንግግር አዳምጫለሁ፡፡

 

በአጠቃላይ ባህላዊው የኮንሶ ከተሞች (ፓሌታዎች) በውስጣቸው የጋሞሌን መንደር በጐበኘሁበት ጊዜ ያየኋቸውንና ከላይ የገለጽኳቸውን ነገሮች አካትቷል። ባህላዊ ስልጣኔ ቀድሞ የገባውና ታታሪ ማህበረሰብ ለመሆኑ ምስክር ነኝ፡፡ ሆኖም እነዚህ ቦታዎች ይበልጥ በቱሪስቶች መጐብኘት ይቀራቸዋል፡፡ የደቡብ ክልል፣ የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን እና የኮንሶ ወረዳ ይህን ድንቅ ተፈጥሮ በተሻለ ደረጃ ለቱሪስት አስጐብኝቶ ታታሪውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

 

ምቹ የማረፊያ ሆቴሎች፣ የማይቋረጥ የሃይል አቅርቦት፣ የኢንተርኔትና የስልክ (የኔትወርክ) መሰረተ - ልማቶች በአግባቡ ከተዘረጉ እንደ ማሪያና አዶልፍ ያሉ የውጨ ቱሪስቶች ስድስት ቀን ብቻ ሳይሆን ስድስት ወር ለመቆየት ይገደዳሉ። የሚያስገድዳቸው ደግሞ የኮንሶ ተፈጥሮ ነው። “ኩርኩፋ የተሰኘው ከበቆሎና ከሞሪንጋ ቅጠል ተቀላቅሎ የሚሰራው ምግብ ስድስት ቀን ብቻ ሳይሆን ስድስት ወር በኮንሶ እንዲቆዩ የሚያስገድድ ነው፡፡ ለዚህ ነው በጽሑፌ መጀመሪያ “ኔትወርክ የለም እንጂ ኔትወርክ ቢኖር ከትሞ ኮንሶ ላይ መቀመጥ ነበር” የሚል ቅኔ ለመዝረፍ የዳዳኝ፡፡ ታዲያ ውቡን የኮንሶ ህዝብ መገለጫ ተፈጥሮዎች በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከ15 ዓመት በላይ እልህ አስጨራሽ ትግል መደረጉን አቶ ገረሶ አጫውተውኛል፡፡ 

 

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በላቸው፤ የመብራት መቆራረጥና የኔትወርክ አለመኖር ትልቁ የካራት ከተማ ችግር መሆኑን አምነው፤ በቀጣይ ከዞኑና ከክልሉ ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለማበጀት እየተጣረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በመብራት፣ በውሃና በዘይት ችግር መማረራቸውንና ስራ መስራት እንዳልቻሉ ገልፀው፤ በችግሮቹ ዙሪያ ህዝቡና አመራሩ በየጊዜው እየተሰባሰቡ ቢወያዩም ችግሩ እየባሰ እንጂ እየተሻለ እንዳልሄደ ተናግረዋል።

 

ምንጭ፡-አዲስ አድማስ ጋዜጣ