አርቲስት ጌታመሳይ አበበ፤‹‹የመሰንቆ ሊቁ››

 

አርቲስት ጌታመሳይ አበበ፤‹‹የመሰንቆ ሊቁ››

 

‹‹የመሰንቆ ሊቁ›› ስንብት

 

አርቲስት ጌታመሳይ አበበ በቀድሞ አርሲ ክፍለ አገር አሰላ ከተማ ልዩ ስሙ አልባሱ አቦጊዮርጊስ በሚባል ቦታ ከአባታቸው መምሬ አበበ ገብሬና ከእናታቸው ከወይዘሮ ተረፍአለች ወልደመድን ሕዳር 28ቀን1935ዓ.ም ተወለዱ። በልጅነታቸው ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ እድል ባለማግኘታቸው አብዛኛውን ጊዜ በእረኝነት እንዳሳለፉ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል። በልጅነት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ባይችሉም፤ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ከሙዚቃ ሥራቸው ጎን ለጎን በገሊላ የህዝብ ትምህርት ቤት የማታ ክፍለ ጊዜ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረዋል።

ከእረኝነቱ በተጨማሪ በሠርግና በተለያዩ በዓላት ላይ የሚያዜሙ አዝማሪዎችን በመመልከት ወደ ሙዚቃ ተሳቡ። በልጅነታቸው ለሙዚቃ መሣሪያ የነበራቸው ፍቅር ከፍተኛ ነበር። በተለይም ለእውቅናቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረውን የመሰንቆ መሳሪያን ገና በልጅነታቸው ራሳቸው ሰርተዋል።

አርቲስት ጌታመሳይ መሰንቆን ፍለጋ በ12 ዓመታቸው ወደ ባሌ ኮብልለው ነበር። ባሌ በነበራቸው ቆይታም በተለያዩ ቦታዎች አዝማሪነትን ሰርተዋል። አዝማሪነቱንም በአዲስ አበባ ሥራ እስኪያገኙ ድረስ ቆይተውበታል።

አርቲስት ጌታመሳይ ከአዝማሪነት ወደ ሙሉ ጊዜ የመድረክ ሥራ ለመምጣት በ1953 ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ቤት ጎራ አሉ። ከዋሽንት ተጫዋቹ አሰፋ ዘገየ ጋር በመሆን በዚሁ ቴአትር ቤት ሦስት ወራት በነፃ አገልግለዋል። ከሦስት ወራት የሙከራ ጊዜ በኋላ በአርባ ብር ደመወዝ ለመቀጠር በቁ። ነገር ግን በቴአትር ቤቱ የቆዩት ለስድስት ወራት ብቻ ነበር።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1955 ዓ.ም በተቋቋመው የባሕል ማዕከል ተቀጣሪዎች አንዱ በመሆን እስከ 1959ዓ.ም አገልግለዋል። አርቲስት ጌታመሳይ በ1967 ዓ.ም ከወይዘሮ በቀለች ሰጠኝ ጋር ትዳር የመሰረቱ ሲሆን፤ ሦስት ወንዶችና አንድ ሴት በአጠቃላይ አራት ልጆችን አፍርተዋል። ትዳር ከመመስረታቸው በፊት አራት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ወልደው ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል። በአጠቃላይ 18 የልጅ ልጆች አይተዋል። አርቲስት ጌታመሳይ በ72 ዓመታቸው ባለፈው ሚያዚያ ወር ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።

 

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ

 

  

Related Topics