በካፋ ብሔረሰብ ዘንድ የለቅሶ፣ የሰርግ፣የጸሎትና የፍቅር ዘፈኖች አሉ፡

ካፋና ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቹ

 

በካፋ ብሔረሰብ ዘንድ የለቅሶ፣ የሰርግ፣የጸሎትና የፍቅር ዘፈኖች አሉ፡፡  በለቅሶ ወቅት ሟችን የሚያወድሱ ጀግንነቱን የሚተርኩ ዘፈኖች ይዘፈናሉ፡፡ በተመሳሳይ የሸካዎች የሰርግ ሥነ-ሥረዓትም በባህላዊ ዘፈኖቻቸው የታጀበ ነው፡፡ እነዚህ ዘፈኖች እንደ ባህሉ በሚቃኙ የባህል ሙዚቃ መሳሪያዎች የሚደምቁ ናቸው፡፡ ጥቂቶችን እንቃኛቸው ከቲንቦ እንጀምር የትንፋሽ መሳሪያው ቲንቦ የካፋን የለቅሶ ሥረዓት በማድመቅ ወደር የሌለው መሳሪያ ሲሆን ከእንጨት የሚሰራ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ለአዋጅ የሚጠቀሙበት ሲሆን ሃይል ያለው ድምጽ በማውጣት ይታወቃል፡፡

 

 

ከንቦ ወይም ከበሮ በብዛት ለለቅሶና ለሰርግ ማጀቢያነት ሲያገለግል፤ በሁሉም ጨዋታዎች ዘንድ ጣልቃ በመግባት ጨዋታውን ከሌላው ባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያ ጋር በመሆን ያደምቀዋል፡፡ ኮኬሎ የሚባለው ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ደግሞ ከእንጨት የሚዘጋጅ ሆኖ በሶስት ወይም በአምስት ክር ድርድሮች የሚበጅ ነው፡፡ ኮኬሎ እህል አሽቶ ወጣቶች ጥበቃ በሚወጡበት ወቅት ቆይታቸው ትዝታ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፡፡

 

ከቅርቀሃ ከሚገኙ የካፋ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ውስጥ ሂኖ እና ሹንቡሮ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ሂኖ ባለ አምስት ድርድር የትንፋሽ መሳሪያ ነው፡፡ እንደ ደቦ ሰርግና የህብረት ጨዋታዎች ወቅት ወንዶች ይጫወቱታል፡፡ ባለ አራት ብሱ የትንፋሽ መሳሪያ የሆነው ቩንቡሮ ብዙ ጊዜ በየትኛውም ቦታ የተለመደ አይደለም፤ ይልቁንም ባህላዊ እምነቶችን በማድመቅ ይታወቃል፡፡ ሌላው የትንፋሽ መሳሪያ ሸረቶ ነው፡፡ በብዛት እረኞች የሚያዘወትሩት መሳሪያ ነው፡፡

 

በካፋ ብሔረሰብ ዘንድ ከእንስሳት ተዋጽኦ የሚዘጋጁ የባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎችም አሉ፡፡ ውድ እንደሆነ የሚነገርለትና አሁን በቀላሉ የማይገኘው ሹመት የተባለው የሙዚቃ መሳሪያ ሲሆን፣ በተለይም ከዋንዛና ከዝሆን ጥርስ የሚዘጋጀ የትንፋሽ መሳሪያ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የሰርግና ሐዘን ሥረዓትን የሚያደምቀው ሹመት በቀላሉ በሁሉም ሰው እጅ የሚገኝ መሳሪያ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከዚህ በተቃራኒው በመጠኑ ትንሽ የሆነውና ከድኩላ ቀንድ የሚዘጋጀው ቲሮ የተባለው የትንፋሽ መሳሪያ እንደ እረኞች ባሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች እጅ በቀላሉ የሚገኙ ናቸው፡፡

ምንጭ፡-tubamegazine