በሺሻ ንግድ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡

ሺሻ ማጨስ ከሲጋራ የበለጠ ጉዳት ያስከትላል!

 

Image result for ሺሻ ማጨስ

 

በሺሻ ንግድ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ሀገሯ ስትመለስ በሻንጣዋ ሸክፋ ካመጣቻቸው ንብረቶቿ አብልጣ በከፍተኛ ጥንቃቄ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባቻቸው የሺሻ እቃዎቿ፤ ዛሬ የሺሻ ንግዷን ያለ ችግር እንድታካሂድ አግዘዋታል፡፡

በወር ስምንት ሺህ ኪራይ በምትከፍልበትና 22 አካባቢ በከፈተችው የሺሻ ማስጨሻ ቤቷ ውስጥ የማይመጣ የለም፡፡ ከምሁር እስከ ወታደር፣ ከተማሪ እስከ አስተማሪ፣ ከነጋዴ እስከ ባለሥልጣን ቤቷን ይጎበኝላታል፡፡ እሷም ታዲያ እንግዶቿን እንደአመላቸው መቀበሉን ተክናበታለች፡፡ ከወጣቱ ወጣት፣ ከሽማግሌው ሽማግሌ፣ ከዱርየው ዱርዬ ሆና ሁሉን እንደ አመሉ ታስተናግዳለች፡፡

የሳምራዊት ደንበኞች ወንዶች ብቻ አይደሉም፣ በተለያዩ የትምህርትና የሥራ ደረጃ ላይ የሚገኙ በሺሻ ሱስ የተጠመዱ ወጣት ሴቶችም ደንበኞቿ ናቸው፡፡ ሳምራዊት ሺሻ ሳታጨስ የዋለችበት ቀን የለም፡፡ ከአንዳንድ ደንበኞቿ ጋር ጫት ለመቃም መሬት ስትይዝ ሺሻ ማጨሻው ከፊቷ አይለይም። የምታጨሰው ሺሻ ጥራቱን የጠበቀ፣ ከውጭ ታሽጎ የሚመጣ ሲሆን ጣዕሙም ሆነ ሽታው ደስ የሚል ስሜትን የሚፈጥር በመሆኑ አጥብቃ እንደምትወደው ትናገራለች፡፡

ሺሻ ማጨስ እንደ ሲጋራ ሁሉ ለተለያዩ በሽታዎች ሊዳርግ እንደሚችል ሲነገር ብትሰማም ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነው ብላ ታምናለች፡፡ “ሺሻ ከተለያዩ የፍራፍሬ አይነቶች የተሰራ ነው፡፡ ምንም አይነት ጉዳትን የሚያስከትል ኬሚካል የለውም፤ ለዚህ ደግሞ ሲጨስ ያለው ሽታና ጣዕም ምስክር ነው” ስትል ትከራከራለች፡፡

እንደ ሳምራዊት ሁሉ አብዛኛው ተጠቃሚ ሺሻ እንደስትሮበሪ፣ ሙዝና ብርቱካን የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች ተቀምሞና ለጤና ተስማሚ ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ ምንም አይነት የጤና ችግር አያስከትልም የሚል እምነት አላቸው፡፡ ይህን የብዙዎችን እምነት የሻረ ዘገባ ኒውዮርክ ታይምስ በቅርቡ አስነብቧል፡፡ ዘገባው እንደሚያመለክተው፤ ሺሻ ትንባሆን ጨምሮ ለሰውነታችን ጎጂ የሆኑ ከ3500 በላይ ንጥረ ነገሮችን አካቶ የያዘ ሲሆን ከእነዚህ ንጥረ ነገሮች መካከል 200 የሚሆኑት ለሰውነታችን እጅግ አደገኛ ናቸው፡፡

ዘገባው በሺሻ ላይ የተደረጉ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ እንዳቀረበው፤ ሺሻ ማጨስ ሲጋራን ከማጨስ በበለጠ ሁኔታ በጤናችን ላይ ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለአርባ አምስት ደቂቃ ሺሻ ማጨስ አንድ ፓኬት ሙሉ ሲጋራን ከማጨስ የበለጠ ጉዳት አለው፡፡ ሺሻ ማጨስ ለአፍና ለድድ ኢንፌክሽን፣ ለቲቢ እንዲሁም ለሳንባ፣ ለአፍና ለአየር ቱቦ ካንሰር የሚያጋልጥ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ከፍተኛ ራስ ምታት፣ የአይን እይታ መደብዘዝ፣ የልብ ህመም፣ የትንፋሽ ማጠርና ስትሮክ የሺሻ ማጨስ ውጤቶች እንደሆኑ አመልክቷል፡፡

ሺሻ በምናጨስበት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ሰውነታችን ውስጥ ስለምናስገባ ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆነው ኦክስጅን በበቂ መጠን እንዳይኖር በማድረግ ለስትሮክ እንደሚያጋልጠን ዘገባው አትቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሺሻ በሚጨስበት ወቅት የማጨሻውን ዕቃ ሰዎች እየተቀባበሉ የሚያጨሱ በመሆኑ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎች በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው እንደሚተላለፉም በዘገባው ተገልጿል፡፡

ምንጭ፡-አዲስ አድማስ ጋዜጣ

 

  

Related Topics