‹‹በሐበሻ ላይ የተጠኑ ኮስሞቲክሶችን ማምረቴ ያስደስተኛል››

‹‹በሐበሻ ላይ የተጠኑ ኮስሞቲክሶችን ማምረቴ ያስደስተኛል››

 

 

ወይዘሪት ሰናይት ተወልደ፣ የጂኤስቲ ፐርሰናል ከየር እና ቢዩቲ ፕሮዳክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዴቨሎፕመንት ማናጀር

ወይዘሪት ሰናይት ተወልደ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተወልደው ካደጉበት አዲስ አበባ እንዳጠናቀቁ የተጓዙት እንግሊዝ ነበር፡፡ በእንግሊዝ የመጀመርያ ዲሪያቸውን በፋርማኮሎጂ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኮስሞቲክ ሳይንስ አግኝተዋል፡፡ ለ11 ዓመታት ያህል በለንደን በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቲአርትስ በመምህርነትም አገልግለዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከመጡ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ በራሳቸው ስም አንድ ምርት አምርተው ማቅረብ ምኞታቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ይኽንንም ለማሳካት በእንግሊዝ አገር እ.ኤ.አ. በ2006 የጀመሩትን ኮስሞቲክ የማምረትና ወደ ስካንዲኔቪያን አገሮች የመላክ ሥራ በኢትዮጵያም በማምጣት የኮስሞቲክ ፋብሪካ ከፍተው እያመረቱ ይገኛሉ፡፡ ወይዘሪት ሰናይት የጂኤስቲ-ፐርሰናል ከየርና ቢዩቲ ፕሮዳክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፕሮዳክሽን ዴቨሎፕመንት ማናጀር ናቸው ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

 

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከመምጣትዎ በፊት በኖሩበት እንግሊዝ የኮስሞቲክ ፋብሪካ ከፍተዋል፡፡  ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ በአዲስ አበባ ተመሳሳይ ፋብሪካ አቋቁመዋል፡፡ ስለሥራዎ ቢያብራሩልን?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- እ.ኤ.አ. በ2006 በእንግሊዝ የኮስሞቲክ ምርቶችን አምርቼ በተለይ ወደ ስካንዲኔቪያን አገሮች እልክ ነበር፡፡ ሰናይት በሚል ብራንድ ነው ምርቶቹ የሚሸጡት፡፡ ይኽንንም ያደረኩት በስሜ አንድ ምርት የማምረት ዓላማ ከበፊት ጀምሮ ስለነበረኝ ነው፡፡ እዛ ያለውን ገበያ ሳየው፣ ለምን አገሬ ገብቼ አልሠራም ብዬ መጣሁ፡፡ አገሬ ስመጣ በእርግጥ ፈቃድ ማውጣቱና ማቋቋሙ ወደ ሦስት ዓመት ያህል ፈጅቷል፡፡ ረዥም  ጊዜ ወስዶብናል፡፡ ማምረት ከጀመርን ሁለት ዓመት ሆኖናል፡፡ በአገር ውስጥ ፍላጎቱ እየጨመረ ስለመጣ፣ እየተመላለስኩ መሥራቴን ትቼ አገሬ ለመግባት በመወሰን ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ ጠቅልዬ በመግባት እየሠራሁ ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግን እንዴት ያዩታል?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- እንደ እውነቱ ዘርፉ ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ የኮስሞቲክ ዘርፍ የመልቲ ሚሊዮን ዶላር ንግድ ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ በዘርፉ የተሰማራነው በጣት የምንቆጠር ነን፡፡  90 በመቶ ያህል የኮስሞቲክ ምርቶች ከውጭ የሚገቡ ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ አገር ውስጥ የምናምርተው ድርሻ አሥር በመቶ ነው፡፡ ይህ በዘርፉ ብዙ ኢንቨስተሮች ሊገቡ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ገበያው አለ፡፡ ሌላው ማየት ያለብን ጉዳይ ለምሳሌ በሻምፖ (ፀጉር መታጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና) ውስጥ ካሉ ንጥረ ነገሮች 50 በመቶ ያህሉ ውኃ ነው፡፡ አንድ ሻምፖ ከውጭ አመጣን ማለት የውጭ ምንዛሪያችንን ውኃ ለመግዛት አዋልነው ማለት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እንደመጣል ይቆጠራል፡፡ በአገራችን ካመረትነው የውጭ ምንዛሪ እንቀንሳለን፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችንም በአገር ውስጥ እንተካለን፡፡ አሁን ላይ ለምርት ግብዓት የሚሆኑንን ብዙዎቹን ንጥረ ነገሮች ከውጭ እናመጣለን፡፡ በሒደት ግን ጥሬ ዕቃዎቹን አገር ውስጥ ለማምረት እናስባለን፡፡ ለወደፊት ጥሬ ዕቃዎችን ከአገር ውስጥ መጠቀም አቅደናል፡፡

 

ሪፖርተር፡- ያለቀለትን የመዋቢያ መጠቀሚያዎች (ኮስሞቲክስ) ከውጭ ማስገባት ከፍተኛ ቀረጥ የሚያስከፍል ነው፡፡ እናንተ ጥሬ ዕቃ አምጥታችሁ ስታመርቱ እንዴት ነው?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- በጥሬ ዕቃ ከሆነ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም አምራቾችንና ኢንቨስተሮችን ለማበረታታት ነው፡፡ አምራች ሲኮን አንዱ ትርፍ ለጥሬ ዕቃ የሚከፈለው ታክስ ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ ያለቀለት ዕቃ ሲገባ ግን ታክሱ ክፍተኛ ነው፡፡ እዚሁ ማምረቱ ከታክስ አኳያም ሲታይ አዋጭ ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- የተለያዩ የኮስሞቲክ ምርቶች አገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ አብዛኞችም ከውጭ በሚመጡት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በዚህ ውስጥ የአገርን ምርት ማስተዋወቁና ማስለመዱ እንዴት ነው?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- እኛ የአንድ ለአንድ ምክክር ላይ እናምናለን፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ በሚካሄዱ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ምርቶቻችንን እናስተዋውቃለን፡፡ ለተጠቃሚው መሸጥ ብቻ ሳይሆን ምክር እንሰጣለን፡፡ ለሽያጭ ሠራተኞቻችን ሙሉ ሥልጠናም ሰጥተናል፡፡ ምክንያቱም የምናመርተው ቅባት፣ ሻምፖ፣ ኮንዲሽነር፣ ፀጉርን ከፀሐይና ከሙቀት የሚከላከል ቅባት፣ የልጆች መታጠቢያና ሎሽኖች ሁሉ በኢትዮጵያዊ ላይ ምርምር አድርገን ነው፡፡ ጥቅም ላይ የዋሉ ንጥረ ነገሮች ምን ጥቅም እንዳላቸውና ለቆዳም ሆነ ለፀጉር ያላቸውን ተፈላጊነት እናብራራለን፡፡ እንዳየነው ተጠቃሚው ሳያነብ የመጠቀም ልምድ አለው፡፡ ለፀጉር ብቻ የሚሆነውን ቅባት፣ ፈሳሽ ስለሆነ ብቻ ለቆዳ፣ ለቆዳ የሚሆነውንም ለፀጉር የሚጠቀም አለ፡፡ እዚህ ላይ ግንዛቤ እንሰጣለን፡፡ ሆኖም ብዙ ይቀረናል፡፡

 

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮስሞቲክ ውስጥ የሚገቡ ንጥረ ነገሮች ለዋጋው ውድነትም ሆነ ርካሽነት እንዲሁም ለምርቱ ጥራት ወሳኝ ናቸው፡፡ አንዱ ምርት አስፈላጊ ከሚባሉት ብዙዎቹን ንጥረ ነገር ሲይዝ፣ አንዱ ደግሞ ጥቂት ይዞ በርካሽ ዋጋ ሲሸጥ ይታያል፡፡ እናንተ የምታመርቱት የንጥረ ነገር ግብዓቱ ምን ይመስላል?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- አገራችን ከውጭ በሚገቡ የኮስሞቲክ ዓይነቶች ተጥለቅልቋል፡፡ የምንከፍለው ዋጋም ውስጡ እንዳለው የንጥረ ነገር ይዘት ነው፡፡ ለምሳሌ ምግብ ውስጥ ምን እንደተጨመረ እናነባለን፡፡ ይህን የምናደርገው የማይስማማን የንጥረ ነገር ዓይነት ካለ ላለመግዛት ወይም ላለመመገብ ነው፡፡ በኮስሞቲክ ሕግ በአሜሪካና በአውሮፓ ደረጃ ለኮስሞቲክ መግባት አለባቸው የተባሉ ንጥረ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህን ከመዋቢያዎቹ ማስረጃ ላይ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ወሳኝ የሆኑ ንጥረ ነገሮች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ነው፡፡ በአገራችን ተጥለቅልቆ የምናየው ብዙ ብግዓቶችን የያዘ አይደለም፡፡ ዋጋው ርካሽ ነው፡፡ በኛ ፋብሪካ አንድ ሻምፖ ለመሥራት ከ15 ንጥረ ነገር በላይ እናደርጋለን፡፡ እያንዳንዱ ንጥረ ነገር የሚገባው ለፀጉር ተስማሚ እንዲሆን ነው፡፡ የነጮች ፀጉር እየቆሸሸ ሲመጣ ቅባታማ ይሆናል፡፡ ለነሱ የሚሠራው መታጠቢያ ውስጥ የሚገባው ንጥረ ነገር ቅባታማውን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የእኛ እየቆሸሸ ሲሄድ እየደረቀ ነው የሚመጣው፡፡ ስለሆነም የሚያለሰልሰው መታጠቢያ ያስፈልጋል፡፡ የኛን ፀጉር መልሶ በሚያደርቅ ሻምፖ መታጠቡ ፀጉሩን ይጎዳዋል፡፡ ለዚህም ነው በነጮች ሳይሆን በአበሻ ላይ የተጠኑ ምርቶች የምናቀርበው፡፡ ንጥረ ነገር መርጠን የምናመርተውም የፀጉሩን ባህሪ አውቀን ነው፡፡ አንድ ሻምፖ ለመሥራት ቢያንስ የሦስት ወር የምርመራ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡

 

ሪፖርተር፡- በምርቱ ከተሰማራችሁ ወዲህ ምን ያህል ጥናቶች አካሂዳችኋል?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- እንግሊዝ አገር በነበርኩበት ጊዜ በምርቶቻችን ላይ ብዙ ጥናቶችን አድርጌያለሁ፡፡ የአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች በሰጡኝ አስተያየት መሠረትም የቀየርኳቸው አሉ፡፡ ለኛ የሚጠቅመን በምርቶቻችን ላይ ያሉ ጉድለቶችን የሚነግረን ነው፡፡ ይህ ምርቶችን ለማሻሻል ይጠቅመናል፡፡ ሆኖም ብዙው ጥሩ ነው የሚል ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- ገበያው እንዴት ነው? ግብዎትን መትተዋል?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- አዎ፡፡ እኔ ያሰብኩት ከውጭ እየተመላለስኩ ልሠራ ነበር፡፡ እንግሊዝ ብሆን በምርምር ሥራውም እገፋበታለሁ ብዬ ነበር፡፡ ሆኖም በአገሬ ልሠራ ካሰብኩት በላይ ፍላጎቱ ስላለና ሥራው ስለተስፋፋ ሙሉ ለሙሉ መጥቻለሁ፡፡ ምርቶቻችንን ለሆቴል በሚሆን መልኩም አዘጋጅተን፣ ሆቴሎች እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የሆቴሎችን ሎጎ አድርገን በትናንሽ መጠን በማዘጋጀት ከብዙ ሆቴሎች ጋር እየሠራን ነው፡፡ ለሆቴሎች የሚሆን ሻምፖ፣ ፈሳሽ ሳሙናና ኮንዲሽነር ከቻይና፣ ዱባይና ህንድ ነበር የሚመጣው፡፡ እኛ ግን አገር ውስጥ አምርተን ለሁሉም እንደሚመች አድርገን እያቀረብን ነው፡፡ 

 

ሪፖርተር፡- 90 በመቶ ያህል ያለቀለት የኮስሞቲክስ ምርት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ገበያ እየገባ ባለበት ሁኔታ እርስዎ ከውጭ መጥተው ኮስሞቲክስ አምርተው ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ መግባትዎን እንዴት ይገልጹታል?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት አግኝተናል፡፡ ሆኖም መለያው (ብራንዲንግ) ላይ መሥራት አለብን፡፡ ‹‹GST›› የሚለውን ማስለመድ ይጠበቅብናል፡፡ ሰው ስሙን ሳይሆን ዕቃውን አይቶ ነው የሚገዛው፡፡ ዩኒሊቨር ወይም ዳቭ ሲባል ሰው ባንዴ እንደሚያውቀው ሁሉ ‹‹GST›› ሲባል እንዲታወቅ እየሠራን ነው፡፡ ‹‹GST›› ምሕፃረ ቃል ሲሆን፣ ገሊላ ሰናይትና ተወልደ የሚለውን ይወክላል፡፡ ገሊላ እህቴ ስትሆን፣ ተወልደ አባታችን ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- (ፓኬጂንግ) ማሸጊያን በተመለከተ ችግሮች እንዳሉ አምራቾች ይናገራሉ፡፡ እርስዎስ የሚሉት አለ? የአገር ውስጥ ግብዓትን መጠቀምን በተመለከተስ?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- በኢትዮጵያ ሥራውን ለመጀመር ስናስብ ዕቅድ የያዝነው ማሽን ለማምጣት ነበር፡፡ ማሸጊያ ዕቃዎች አገር ውስጥ ይኖራሉ ብለንም ነበር፡፡ ሆኖም እየዞርን ስናይ የምንፈልገው ዓይነት ማሸጊያ (ፕላስቲክ) ማግኘት አልቻልንም፡፡ ስለዚህ የራሳችንን ሞልድ (ቅርፅ ማውጫ) አምጥተን ማሸጊያ ለሚሠራ ካምፓኒ ሰጥተን ለኛ ብቻ የሚውል ፕላስቲክ እያመረተልን ነው፡፡ ይህ ያላሰብነው ወጪ ነው፡፡ ሌብሊንግ (ስለምርቱ መግለጫ) ከኬንያ ነበር የምናመጣው፡፡ አሁን ግን ሌብሊንግ ካምፓኒዎች አገራችን ስለመጡ ከዚሁ መውሰድ ጀምረናል፡፡ ጥሬ ዕቃ አሥር በመቶ ያህል ከአገር ውስጥ እንጠቀማለን፡፡ 90 በመቶ ከውጭ ነው፡፡ ወደፊት ግን ብዙውን ግብዓት ከአገር ውስጥ ለማድረግ እናስባለን፡፡ አሁን ላይ ቦታኒካል ጋርደን ካላት ሰው የተወሰነ ንጥረ ነገር እየወሰድን ነው፡፡ የቆዳ ቅባቶች ላይ ስንገባም የአገር ውስጥ ግብዓት ተጠቅመን እንሠራለን የሚል ዕቅድ አለን፡፡

 

ሪፖርተር፡- የፊት ቆዳ መጠበቂያዎችና መዋቢያዎች ላይ ለመሥራትም አቅዳችኋል?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ዕቅድ አለን፡፡ አሁን ብራንዲንጉን ማስተዋወቅ ላይ በቅድሚያ መሥራት አለብን፡፡ የሕፃናት መታጠቢያ፣ ሎሽንና ቤቢ ኦይል (ፈሳሽ የሰውነት ቅባት) ማምረት ጀምረናል፡፡ ከዓመት በፊት ለሰውነት የሚውል ሎሽን አስተዋውቀናል፡፡ እንደ ቅቤ የሚያገለግልና ቅባትም እያመረትን ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ሠራተኞች አሉዋችሁ? ምርትስ ትቸረችራላችሁ?

 

ወይዘሪት ሰናይት፡- አሥር ቋሚ ሠራተኞች አሉን፡፡ በአጠቃላይ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች በሥራው ይሳተፋሉ፡፡ ምርቶቻችንን ለአከፋፋዮች እንሰጣለን እንጂ እኛ በራሳችን አንቸረችርም፡፡

 

ምንጭ ፡- ሪፖርተር

 

 



 

Related Topics