‹‹ድራፍት እንደወረደ-ጤና-አዳም ይኑረው!››

ድራፍት በጤና- አዳም

 

beer

 (ሀ)

‹‹ድራፍት እንደወረደ-ጤና-አዳም ይኑረው!››

 

ድራፍት የመጠጣትችግሩ ምን መሰላችሁም? ቀጂው ፊት ካልሆናችሁ ጭላጭ ሊመጣላችሁ ይችላል፡፡ ‹‹እንደወረደ!›› እያለ ሕዝበ-አዳም ጥማት ባቃጠለው ጉሮሮው የሚጨኽው ወዶ መሰላችሁ? ሲቀጥል ባልታጠበ ብርጭቆ ሊቀርብላችሁ ይችላል፡፡ ወይ ደግሞ ቀጂው አለያ አስተናጋጆቹ ጉንፋን ሊይዛቸው ይችላ ፡፡ አፍንጫን እየጠረጉ መቅዳትና ማስተናገድ ብርቅ ነው እንዴ? በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ከድብልቅ ነዳጅ ቀጥሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሪሳይክል እየሆነ ያለው ጉንፋን ነው፡፡

 

በፊት በፊት ‹‹ለማንኛውም ሎሚ መድሃኒት ነው ስለሚባልም ሆነ እንደልብ ስለሚገኝ ‹‹ድራፍት ከሎሚ ጋር!›› ይታዘዝ ነበር፡ ዛሬ ማን ልብ ያለው ነው ለድራፍት ሎሚ የሚያቀርብላችሁ? ሎሚ ለድራፍት ቀርቶ ለውርወራም ጠፍቷል፡፡ ‹‹ገና ሽታውም ይናፍቅሃል!›› ይሉሃል አስተናጋጆች ድራፍት ከሎሚ ጋር ብታዛቸው፡፡ለዚህም ይመስላል ለመጋኛውም ለቁርጠቱም የምትወሰደውን ጤና- አዳም ድራፍት ውስጥ ጨምሮ መጠጣት የተጀመረው፡፡

 

ጉዳዩ የት ሠፈርና መቼ እንደተጀመረ ጥናት አላኬሄድንም፡፡ በነሲብ ስንገምት ግን ጉዳዩ ከጀበና ቡና መስፋፋት ጋር የተጀመረ ሳይሆን አይቀርም ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናል፡፡ ማን ያውቃል አንዱ ሞቅ ያለው ጠጪ ለቡና የመጣለትን ጤና-አዳም ድራፍቱ ውስጥ ጨምሮት በዚያው ተለምዶ ሊሆን ይችላልል፡፡ ግን ማለፊ ሀሳብ ይመስላ፡፡ ‹‹ድራፍት እንደወረደ-ጤና-አዳም ይኑረው!›› ልንል ነው እንግዲህ፡፡

 

(ለ) የቢራዎች ጦርነት (‹‹ውድድር ለዘላም ይኑር!››)

 

የምጣኔ ሀብት (Economics-101) እንደሚለው በአንድ የገበያ አውድ ውስጥ ሌሎች ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው ብዙ ሻጮችና ገዥዎች ሲኖሩ ገበያው በራሱ ጊዜ ይሳለጣል፡፡  በዚህ ዓውድ ብዙ ጠማቂዎችና ነፍ ጠጪዎች ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዓለማቀፉ ቢራ ጠማቂ ሄኒኬን ዋልያ ብሎ የሰየመውን ቢራ ይዞ ከመጣ ወዲህ የቢራ አጠጣጥ አውዱ የተቀየረ ይመስላል፡፡ አስተዋዋቂዎቹ እንደሚነግሩን ፋብሪካው በቀን ከ1.5 ሚሊዮን ጠርሙስ በላይ ቢራ ያመርታል፡፡ እንደሚታየው ጠጪውም ምርቱን ለመጨረስ ይመስላል እንደ ነዳጅ ማደያ 24 ሰዓታት መቅዳቱን ተያይዞታል፡፡

 

በዚህ ደራሽ የቢራ ማዕበል የተጥለቀለቁ የሚመስሉት ነባር ፋብሪካዎች በጎርፉ እንዳይበሉ መፍጨርጨሩን የተያያዙት ይመስላል፡፡ ከኢትያጵያ የነፃነት ተጋድሎ ጋር ሥሙ ተያይዞ የሚነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ (ቢጂአይ) ከአነስተኛ ቅናሽ እስከ ግዙፍ ማስታወቂያ (Promotion) ፍልሚያውን የተያያዘው ይመስላል፡፡ እኛ ምን አገባን እነሱ  ሲራገጡ በሳቅ እየፈረስን ቢራ በቅናሽ ለሸጠልን ብርጭቆአችንን እናጋጫለን፡፡ ‹‹ዘላቂ ሞቅታ እንጂ፤ ዘላቂ ወዳጅነት የለም!›› እዲል መጽሐፈ- ቅምቀማ፡፡ ‹‹ውድድር ለዘላም ይኑር!››

 

ያው በማስታወቂያ እንደምንሰማው አንዳንድ አገርኛ ቢራ ጠማቂዎች መጣን መጣን እያሉ ሲሆን ያሉትም ልብሳቸውንም ሆነ አይነታቸውን በመቀያየር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ምክናያታዊ ያልሆነ የብራንድ ትውውቅ ‹‹ለዘመን›› የነበረን ቃና ስለሚያጠፋ መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ ግፋሲ ሲልም ለጠላዎቻቸው ሀገራዊ ስያሜዎችን መስጠቱ አዋጪ ቢዝነስ ይመስላል እንላን፡፡ ዋልያን ልብ ይሏል፡፡

 

(ሐ) ፈር የለቀቀው የቢራ አሻሻጭነት (በሀላፊነት እናሻሽጥ)

 

ዛሬ ዛሬ የቢራ አሻሻጭነትና የስፖርት ፕሮግራሞች አንድና አንድ የሆኑ ይመስላል፡፡ በተለይ አንዳንዶቹ ልሳናቸው እስኪዘጋ ድረስ ግፋ ሲልም የማስታወቂያም ሆነ የስፖርት ሥነ – ምግባርን በሚጋፋ ሁኔታ ልክ እየጠጡ የሚያጣጥሙ እስኪመስልባቸው ድረስ አሻሻጭነቱን እያጧጧፉ ይገኛሉ፡፡ እነሱ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ እያስተዋወቁ ልክ በትናንሽ ፊደላት እንደተጻፉት ቃላት በሃላፊነት እንጠጣ ይሉናል ባለቀ ትንፋቸሻቸው፡፡ ነውር ነው፡፡ እናም እንላለን- በሀላፊነት እናሻሽጥ!

ምንጭ፡-/aglegele