በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙት 16 ብሔረሰቦች አንዱ ኛ

የኛንጋቶም ሦስቱ አስደናቂ ምሰሶዎች

 

 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙት 16 ብሔረሰቦች አንዱ ኛንጋቶም ነው፡፡ በኦሞ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚኖሩት ኛንጋቶሞች የተለያዩ ማኅበራዊ አኗኗሮች አሏቸው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከእርሻቸው የሚያገኙት ማሽላ፣ በቆሎና ባቄላን ነው፡፡ ከኦሞ ወንዝም አሳን ያጠምዳሉ፡፡

 

ከፊል አርብቶ አደር የሆነው የኛንጋቶም ማኅበረሰብ ከእንስሳት ከሰብል ምርትና ከርስ በርስ ግንኙነት አንፃር ያሉትን ሦስት አስደናቂ ምሰሶዎች ተመራማሪዋ ጁሊያ ፊዝትነር ‹‹የኛንጋቶም ከፊል አርብቶ አደር እይታ›› በሚል ርዕስ እንደሚከተለው አብራርታዋለች፡፡

 

ምሰሶ አንድ - እንስሳት

 

የኛንጋቶም ባህል ከእንስሳት እርባታ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ሲሆን ለኛንጋቶም የቤት እንሰሳ ማለት የባህላቸው አንዱ ምሰሶ ነው፡፡

 

‹‹የኛንጋቶም ባህል ማለት የከብት ባለቤትነት ነው፡፡ ከብቶቻችንን ካጣን ባህላችንንም አጣን፡፡›› ሲሉም ይናራል፡፡

 

እንስሳት በኛንጋቶም ሕይወት ውስጥ በተለይም የቀንድ እንስሳት ማለት ለወተት፣ ሥጋና ሌጦ ምርት ጥቅም ከሚውሉ እንስሳት በላይ ናቸው፡፡ ከሀብት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ከበሬታም የሚለካው አንድ ቤተሰብ በሚኖረው የእንስሳት ብዛት ነው፡፡ የጥሎሽ ክፍያ እንስሳት ናቸውና ለጋብቻ ቅድመ ሁኔታ ይቀርባሉ፡፡ እንደማኅበረሰቡ አተያይ በጥንቃቄ የሚደረግ የሚስት ምርጫና የእንስሳት ባለቤትነት የወንዱ መለኪያ ነው፡፡

 

እንደ ኛንጋቶም ትውፊት፣ ‹‹ጠንካራ ወንድ ከብቶቹን ይዞ ርቆ ይሄዳል፡፡ ጠላትን ይፋለማል፣ ረሀብ አይፈራም፡፡ ከምንም በላይ ከብቶቹን ይወዳል፡፡››

 

ይህም ፅናትን እንደ አዎንታዊ የጠንካራ ወንድ መገለጫ ይገለጽበታል፡፡ ከረሀብ ጋር ተያይዞ የሚመጣ በሽታን በጽናት መጋፈጥ መቻልም አንዱ የጥንካሬ መገለጫ ነው፡፡ ኛንጋቶሞች ከቀንድ እንስሳት ጎን ለጎን ጥቂት አመንዣኪዎችም (በግና ፍየል) አላቸው፡፡ እነርሱም በተለይ በችግር ጊዜ ለዓይነት ልውውጥ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን የበግ፣ የፍየልና የቀንድ እንስሳት ልውውጥን ለማስቀረት በተቻለ መጠን ጥረት ይደረጋል፡፡

 

በእረኝነት መሰማራት ከጦርነትና ራስን እንደ ጦረኛ ከማየት ጋር የተቆራኘም ነው፡፡ በተለይ የግጦሽ መሬት ለግጭት የተጋለጠ ነውና ከእንስሳት ቀጥሎ ሁለተኛው አስፈላጊ የወንድነት መገለጫ ጠመንጃ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተሳካ ሁኔታ እንስሳትንና ማኅበረሰቡን ከጥቃት መጠበቅ አንዱና በጣም አስፈላጊ የወንድ ሚና ነው፡፡

 

ከእህል በተጨማሪ የእንስሳት ተዋጽኦዎች በዕለታዊ ፍጆታ ውስጥ አስፈላጊ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ትናንሽ አመንዣኪዎች (ፍየልና በግ) በአካሙ ወቅት (በድርቅ/በረሀብ ወቅት) ለእርድ ያገለግላሉ፡፡ በዚህ ወቅት የቀንድ ከብቶች ወደሩቅ ቦታ ሲወሰዱ ጥቂት ፍየልና በጎች ከአዛውንቶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ጋር መንደር ውስጥ ይቆያሉ፡፡ በድርቅ ወቅት ፍየል (ሻል ባለ ጊዜ በጎችም በጣም አስፈላጊ ናቸው፤ ለምሳሌ የዝናብ ልመና ሥነ ሥርዓት)፡፡ የቀንድ ከብት የሚታረደው እንደ ትላልቅ ሥርዓታዊ ወጎችና ሠርግ ላሉ በጣም ልዩ ለሆኑና ለተመረጡ ጉዳዮች ብቻ ነው፡፡ ለምግብነት እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑትና ብዙ ጊዜም ተቀላቅለው የሚቀርቡት የላም ወተትና ደም ናቸው፡፡ ከሥጋ ጎን ለጎን ቅቤ ልዩ ማኅበራዊ እሴትን ያስተላልፋል፡፡ እነዚህ የዕለት ተዕለት ምግብ ናቸው፡፡ በዋናነት ግን ለአዛውንቶችና በጣም ለተከበሩ ሰዎች የሚቀርቡ የምግብ ዓይነቶች ናቸው፡፡

 

ለኛንጋቶሞች እንስሳት የማንነት መለያ ናቸው፡፡ በሴቶች የሚለበሰው የበግና የፍየል ሌጦ ከየትኛው ጎሳ መሆናቸውን እንዲሁም የጋብቻ ሁኔታቸውን ይጠቁማል፡፡ የእንስሳት ቀለምና የመንጎች ቅንብር አባወራው በማኅበረሰቡ ውስጥ ስላለው ደረጃ ግልጽ የሆነ መረጃን ይሰጣሉ፡፡

 

እንደ ጁሊያ ፊትዝነር ማጠቃለያ፣ ከኢኮኖሚያዊ ተፈላጊነታቸው በተጨማሪ ሁሉም እንስሳት በተለይ የቀንድ ከብቶች ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ትርጉም አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ የእንስሳት ተዋጽኦ ባለቤት መሆን በራሱ፣ እንዲሁም ለፍጆታና ለጥቅም ማዋል የከፊል አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ማንነት ዋነኛ ክፍል ነው፡፡

 

ምሰሶ ሁለት - የሰብል ምርት

 

ኛንጋቶሞች ዓመታዊ የእህል ምርት እንቅስቃሴያቸውን በሁለት የተለያዩ የግብርና ዑደቶች ማለትም በዝናብና በወንዝ ጎርፍ ላይ መሥርተዋል፡፡ የዝናብ እርሻ በበልግ ዝናብ (አኮፖሮ) እገዛ በየካቲትና በግንቦት መካከል ይከናወናል፡፡ የወንዝ ዳር ደለል ግብርና የሚከናወነው በክረምት ወራት (ከሐምሌ እስከ መስከረም) በደጋማው አካባቢ በሚዘንበው ዝናብ ምክንያት የኦሞ ወንዝ ጎርፍ ይዞት በሚመጣው የወንዝ ዳርቻ ለም አፈር ላይ ነው፡፡

 

ሁለቱ የግብርና ዑደቶች የአስተራረስ ዘዴ ጥቂት ልዩነት አላቸው፡፡ እጅግ በጣም አስፈላጊዎቹ አዝርዕት ማሽላ፣ ባቄላና በቆሎ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የወንዙ ዳርቻ ትምባሆ፣ ዱባና ቅል ለማብቀል ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በአነስተኛ መጠን ከሚመረቱት ባቄላና በቆሎ ይልቅ ማሽላ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ከዚያም በላይ በባህላዊ ምክንያት የተለየ ተፈላጊነት አለው፡፡ ኛንጋቶሞች ማሽላን ቅዱስ ነው ይላሉ፡፡ ለተለያዩ ሥርዓታዊ ወግም ይጠቀሙታል፡፡ ከእንስሳቱ ባሻገር የማሽላ መኖርና ለፍጆታ መዋል ኩራታቸውና የማንነታቸው መገለጫ ጭምርም ነው፡፡

 

‹‹የምናገኘው ሁሉ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ማሽላ መብላት ካልቻልን ረሀብ ይሰማናል እውነተኛ ኛንጋቶምነትም አይሰማንም፤›› ይላሉ፡፡

 

በሌላ በኩል በቆሎና ባቄላ በሦስት ወር ከሚደርሰው ማሽላ ይልቅ በአጭር ጊዜ (በሁለት ወር) ይደርሳሉ፡፡ ይህም የማሽላ ምርት ከመድረሱ በፊት የረሀቡን ጊዜ ለማሳጠር የሚያገለግሉ አስፈላጊ የሰብል ዝርያ ያደርጋቸዋል፡፡

 

ምሰሶ ሦስት - የኛንጋቶም ‹‹የመረዳዳት ባህል››

 

በምሰሶ ሁለት እንደተገለጸው የእንስሳት እርባታና የሰብል ምርት የኛንጋቶም ማኅበረሰብ የማንነት ክፍል ናቸው፡፡ የእንስሳት እርባታና የሰብል ምርት ከምግብ ዋስትና፣ ከባህልና ራሳቸውን ከሚገምቱበት ሚዛን አንፃር ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ ከተገለጸው አስፈላጊነታቸው ባሻገር እንስሳትና ማሽላ ወዳጅነትን ለመመሥረት አስፈላጊ መሣሪያ ናቸው፡፡ ኛንጋቶሞች እንስሳትና ማሽላን በመስጠትና በመቀበል በማኅበረሰባቸው ውስጥ ጠንካራ ማኅበራዊ የግንኙነት መረብን ይፈጥራሉ፡፡ ይህ የመስጠትና የመቀበል ግንኙነት በረሀብና በችግር ጊዜ አስፈላጊ መደጋገፍን አምጥቷል፡፡ ማኅበረሰቦቻቸውና አባሎቻቸው በተለያየ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ላይ ስለሚገኙ ነዋሪዎቹ የሚገጥሟቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎችም እንዲሁ የተለያዩ ናቸው፡፡

 

አካሙ (ድርቅ) ሁሉንም ኛንጋቶሞች በተመሳሳይ ደረጃ አያጠቃም፡፡ ከፊሎቹ ኛንጋቶሞች በወንዝ ዳር እርሻ ላይ ሌሎቹ ደግሞ በእንስሳት እርባታና በዝናብ ላይ የተመሠረተ እርሻ የተደገፉ ናቸው፡፡ በድርቅ ወቅት የልውውጥ ግንኙነት ሕይወትን የማቆያ ትልቁ መንገድ ነው፡፡ ይህን በችግር ጊዜ የሚፈጠረውን መረዳዳት እንዲህ ይገልጹታል፡፡

 

‹‹ወዳጅ ሕይወትህን ይታደጋል፡፡ በድንገተኛ አደጋ ጊዜ ልትቀርበው ትችላለህ፤ እርሱም በአህያህ ማሽላ ይጭንልሀል፡፡ ምንም ነገር አይጠይቅህም ምክንያቱም አንተም እንዲህ እንደምታደርግ ያውቃልና፡፡››

 

በሰፈር ውስጥ ሁሉም የዕቃ ልውውጥና ስጦታ (የምግብ ዕርዳታን ጨምሮ) በወዳጆችና በዘመዳሞች መካከል ይከፋፈላል፡፡ እርድ ሲደረግ አባወራው በማኅበረሰቡ ውስጥ ከሚገኙ ወዳጆቹ ጋር ይካፈላል፡፡

 

መደበኛ ምግብ እንኳን አቲያም በሚባለው በማኅበረሰቡ መካከለኛ የመሰብሰቢያ ስፍራ በአንድነት ይበላል፡፡ እያንዳንዱ ወንድ እንደ ሚስቶቹ ቁጥር ብዛት በቅል ምግብ ሞልቶ ያበረክታል፡፡ አዛውንቶች ከወጣቶች በለጥ ያለ ይሰጣሉ፡፡ በንጽጽር አልፎ አልፎ በሬ አርደው አዛውንቶችን የሚጋብዙት ወጣት ወንዶች ናቸው፡፡ ይህም እንደነሱ አገላለጽ፣ ‹‹ለወጣት ወንድ ለአዛውንቶች በሬ ማረድ ክብር ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ለመከበርና ለመባረክ አስፈላጊ ነው፡፡››

 

ስለዚህ የተገኘው ምግብ ሁሉ በአካባቢ እንዲሁም በመንደር ደረጃ ይከፋፈላል፡፡ የምግብ እደላው የኛንጋቶም ኅብረተሰብን ደኅንነት ሚዛናዊ ለማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የኛንጋቶሞች የመካፈል ባህል አስቸጋሪና አጠራጣሪ ሁኔታ ሲገጥማቸው ራሳቸውን የሚያስተካክሉበት ትልቁ መሣሪያቸው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ባህላዊ ሁኔታ የኛንጋቶም ማኅበረሰብ የሚታወቅበትና ከዕለታዊ ኑሮአቸው ውስጥም የተዋሐደ ሚናን የሚጫወት ነው፡፡ ሰጥቶ መቀበል ከላይ እስከታች ያለ የመቋቋሚያ ዘዴና የከፊል አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ማንነት ዋና ክፍል ነው፡፡

ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ