የመድኃኒት አለርጂ መድኃኒት ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የሚመጣ ያልተለመደና

የመድኃኒት አለርጂ ምን ማለት ነው?

 

Image result for አለርጂ

 

የመድኃኒት አለርጂ መድኃኒት ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የሚመጣ ያልተለመደና ያልተፈለገ የጐንዮሽ ጉዳት ነው፡፡

የተለያዩ ዓይነት የመድኃኒት አለርጂዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ይህም ከቀላል የቆዳ ላይ ሽፍታ እስከተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን የሚያጠቃ ከባድ አለርጂ ሊሆን ይችላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች የሰውነት ክፍሎች ይልቅ አለርጂ በቆዳ ላይ ይታያል፡፡ የመድኃኒት አለርጂ ምልክቶችን ማወቅ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕይወትን አደጋ ላይ ሊጥሉ ስለሚችሉ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የመድኃኒት አለርጂ የሚከሰተው መድኃኒትን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲወስዱ ላይሆን ይችላል፡፡ መድኃኒቶች ከአንድ ጊዜ (ከአንድ ዶዝ ለምሳሌ ከአንድ እንክብል) በላይ ሲወሰዱ የሚያጋጥም ነገር ነው፡፡ ይህንን ስንል ግን በመድኃኒት ምክንያት የሚመጡ ጐጂ ባህሪያት ወይም የጐንዮሽ ጉዳቶች ሁሉ አለርጂ ማለት እንዳልሆኑ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ከሚያጋጥሙ የጐንዮሽ ጉዳቶች ውስጥ አለርጂ የሚሆኑት አብዛኛውን ጊዜ ከ10 በመቶ ያነሱ ናቸው፡፡

 

የመድኃኒት አለርጂ መንስኤዎች

የመድኃኒት አለርጂ የሚከሰተው የምንወስደውን መድኃኒት ሰውነታችን እንደ ባዕድ ነገር ቆጥሮ ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ነው፡፡

 በተደጋጋሚ አንድን መድኃኒት መጠቀም፣ መድኃኒቱን ከፍ ባለ መጠን መጠቀም፣ በአፍ ከመውሰድ ይልቅ መድኃኒት በክትባት መልክ መውሰድ፣ በቤተሰብ ውስጥ አለርጂ የገጠመው ሰው መኖር፣ ለተለያዩ ምግቦች /እንቁላል፣ ዓሣ/ አለርጂ መሆን በመድኃኒት ምክንያት ለሚመጣ አለርጂ ተጋላጭነት እንዲጨምር ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የመድኃኒት አለርጂ እንዲከሰት ከሚያደርጉ መድኃኒቶች ውስጥ ለመጥቀስ ያህል የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች /አስፕሪን፣ አይቡፕሮፌን/፣ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች/ፔኒሲሊን፣ ቴትራሳይክሊን/ ወዘተ ይገኙበታል፡፡

 

የመድኃኒት አለርጂ ምልክቶች

የመድኃኒት አለርጂ ሲፈጠር የተለያዩ ዓይነት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ የአለርጂ ምልክቶች እንደ መድኃኒቱ ዓይነት እና ለመድኃኒቱ የመጋለጥ መጠን ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ የተለመዱት የመድኃኒት አለርጂ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

–    የቆዳ ሽፍታ

 

–    ትኩሳት

 

–    የጡንቻና የመገጣጠሚያ አካባቢዎች ህመም

 

–    የብሽሽት እብጠት (Lymph Node Swelling)

 

ከመድኃኒት ውጪ ያሉ አለርጂዎች አለርጂ ለሚሆነው ነገር በተጋለጥን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከሰቱ ሲሆን የመድኃኒት አለርጂ ግን ብዙውን ጊዜ መድኃኒቱ ከተወሰደ ከቀናት ወይም ሳምንታት በኋላ ይታያሉ፡፡ ሌላው የመድኃኒት አለርጂ ዓይነት ሕይወትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችልና በጤና ተቋም ደረጃ በአፋጣኝና በድንገተኛነት መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ አናፊላክሲስ ወይም አናፊለክቲክ ሪአክሽን የሚባለው ዓይነት ነው፡፡

 

የዚህ ዓይነቱ አደገኛ አለርጂ መገለጫዎች በቆዳ ላይ የማሳከክ ስሜት፣ መቅላት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ራስን መሳት፣ ፈጣን ወይም የተዛባ የልብ ምት፣ የፊት፣ የከንፈር፣ የምላስ፣ እጅ፣ እግር ወይም የመገጣጠሚያዎች እብጠት ሲሆኑ የዚህ ዓይነቱ አለርጂ መድኃኒቱ በተወሰደ በአራት ሰዓታት ውስጥ ሊታይ ይችላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን በሰከንዶች ወይም በደቂቃዎች ውስጥ ይከሰታል፡፡

 

የጤና ባለሙያ ዕርዳታ የሚያስፈልግዎ መቼ ነው?

የሚወስዱት መድኃኒት ምልክቶቹ ቀለል ያሉ ከሆኑ ወደ ሌላ መድኃኒት ሊቀየርሎት፣ መድኃኒቱን እንዲያቋርጡ ሊደረግ ወይንም ምልክቶቹን የሚያጠፋ መድኃኒቶች ሊታዘዝሎት ይችላል፡፡ በተለይ እንደ ትኩሳት፣ ማስመለስ የመሳሰሉት ምልክቶች ከታየብዎት ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይገባዎታል፡፡

 

ምርመራዎች

ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የመድኃኒት አለርጂ ሊታወቅ /ሊለይ/ የሚችለው ታማሚው ላይ በሚታዩት ምልክቶች ሲሆን የጤና ባለሙያዎች እነዚህን ምልክቶች በሥልጠና ያውቋቸዋል፡፡ አልፎ አልፎ የደም ምርመራ እና ሌሎችም ምርመራዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡

 

የመድኃኒት አለርጂ ሕክምና

ከጤና ባለሙያ በሚገኝ ምክር አንዳንድ ቀለል ያሉ የአለርጂ ምልክቶች በቤት ውስጥ ሊታከሙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፡– በቆዳ ላይ ለሚወጣ ሽፍታ በቀዝቃዛ ውኃ ገላን መታጠብና ቀለል ያሉ ልብሶችን መልበስ ይጠቅማል፡፡ የማሳከክ ስሜትን ለመቀነስ ደግሞ የጤና ባለሙያን አማክሮ መድኃኒቶችን መውሰድ ይቻላል፡፡ ከበድ ላሉ የመድኃኒት አለርጂ ምልክቶች /ለምሳሌ፡– አናፊላክሲስ/ በሚከሰቱበት ጊዜ ግን ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም መሔድ ይገባል፡፡

 

የመድኃኒት አለርጂን በመድኃኒት ማከም ካስፈለገ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አስቀምጦ መመልከት ይቻላል

 

1.    ቀለል ያሉ የመድኃኒት አለርጂ ምልክቶች /አልፎ አልፎ የቆዳ ላይ ማሳከክና ሽፍታ/ ዓላማው በመድኃኒቱ ምክንያት የታየውን ችግር እና አለርጂ ማስቆም ሲሆን Antihistamine /አንቲሂስታሚን/ በተባሉት የመድኃኒት ክፍል ሥር የሚገኙ መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡ ብዙውን ጊዜም አለርጂ ያስከተለው መድኃኒት እንዲቋረጥና በምትኩ ሌላ እንዲታዘዝ ይደረጋል፡፡

 

2.    ጠንከር ያሉ የመድኃኒት አለርጂ ምልክቶች /የሰውነት ሙሉ በሙሉ ሽፍታ እና ማሳከክ/ እና ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ከባድ የመድኃኒት አለርጂ ምልክቶች /የትንፋሽ ማጠር፣ ራስን መሳት/ በዚህ ጊዜ አለርጂውን ያስከተለው መድኃኒት ወዲያውኑ እንዲቆም የሚደረግ ሲሆን የተፈጠሩትን አካላዊ ችግሮች የሚያሽሉ መድኃኒቶች ለታማሚው ይሰጣሉ፡፡ አለርጂው በጣም ከባድ ከሆነ ጤና ተቋም ውስጥ ተኝቶ መታከም የግድ ሊሆን ይችላል፡፡

 

የመድኃኒት አለርጂን እንዴት መከላከል ይቻላል?

 

የመድኃኒት አለርጂን ለማስቀረት የሚያስችል መንገድ ባይኖርም እንኳን ለመድኃኒት አለርጂ የመጋለጥ መጠንን መቀነስ ይቻላል፡፡ ማንኛውም መድኃኒትን የሚወስድ ግለሰብ ታዘለት የሚወስደውን መድኃኒት ምንነትና የጎንዮሽ ጉዳቶቹ ምን ምን እንደሆኑ ከጤና ባለሙያ ጠይቆ መረዳት ይገባዋል፡፡ በመድኃኒቱ ምክንያት የአለርጂ ምልክቶች ያጋጠመው እንደሆን መድኃኒቱን በራሱ ከማቋረጥ ይልቅ ወደ ጤና ተቋም መሔድ ይኖርበታል፡፡

 

ቀደም ሲል የወሰዱት መድኃኒት የአለርጂ ምልክት አምጥቶብዎት ከነበር በድጋሚ መድኃኒቱን መውሰድ ስለሌለብዎት መድኃኒቱ ደግሞ እንዳይታዘዝልዎት ለጤና ባለሙያዎ ያሳውቁ፡፡

 

ለአንድ ታካሚ ታዞ የነበረ መድኃኒት አለርጂ ቢያስከትልበትና በሌላ ጊዜ ከሌላ የጤና ተቋም ቢሔድ መድኃኒቱ መልሶ እንዳይታዘዝለት ለማድረግ የአለርጂ መታወቂያ ካርድ በአገር ደረጃ ተዘጋጅቶ በየጤና ተቋማቱ ይገኛል፡፡ የዚህ መታወቂያ ካርድ ዋና ዓላማ ማንኛውም አለርጂ የገጠመው ታካሚ አለርጂ ያስከተለበትን መድኃኒት ስም በመታወቂያ ካርዱ ላይ በጤና ባለሙያ እንዲጻፍለት በማድረግ ለግሉ እንዲይዝ እና በማንኛውም በሚሔድበት የጤና ተቋም መድኃኒት ሳይታዘዝለት በፊት ካርዱን ለጤና ባለሙያው በማሳየት በድጋሚ በአለርጂው እንዳይጠቃ መካላከል ይቻላል፡፡

 

ምንጭ:የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን)

 

  

Related Topics