ብዙዎች አብርሃም አስመላሽን በኮሜዲነት ያውቁት ይሆናል።

ዝክረ አብርሃም አስመላሽ

 

Image result for አብርሃም አስመላሽ

ብዙዎች አብርሃም አስመላሽን በኮሜዲነት ያውቁት ይሆናል። አብርሃም ግን ቀልደኛ ብቻ ሳይሆን ሁለገብ አርቲስትም እንደነበር በተለያዩ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ድራማዎች ላይ በሰራቸው ስራዎች አስመስክሯል። የገጠር አካባቢ ዘዬዎችን በማስመሰል በሚጫወታቸው ገፀ ባህሪያት አድማጭና ተመልካችን ያዝናና ነበር። አብርሃም አስመላሽ ዛሬ በሕይወት የለም። ዳሩ ግን እንዲህ ለሕዝብ ውለታ የዋለ ሰው የሕዝብ ነውና ማንም በስራዎቹ ያስታውሰዋል። ዛሬ ስለ አብርሃም እንድናስታውስ የሚያስገድደን ደግሞ ከዚህ ዓለም በአካለ ሥጋ የተለየን ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት በዛሬዋ ቀን ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር።

ሚያዝያ 16 ቀን 1958 ዓ.ም የተወለደው አብርሃም አስመላሽ ትውልዱና እድገቱ አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። አብርሃም በኮሜዲ ሥራዎቹ የማህበረሰቡን ህይወት በተዋዛ አንደበት እያቀረበ ያዝናና ነበር። ከልጅነቱ ጀምሮ የኪነ ጥበብ ፍቅር ያደረበት አብርሃም ልጅ እያለ ነው።በልጅነቱም ጓደኞቹን እየሰበሰበ መጫወት ያዘወትራል። በ22 ዓመቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ «እረኛው» የሚል መነባንብ ያቀርብ ነበር። በመስከረም 2005 ዓ.ም ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የአዲስ አበባ ልጅ ሆኖ የገጠር ዘዬዎችን እንዴት መጫወት እንደቻለ ተጠይቆ ሲመልስ ከክፍለ አገር ለንግድ የሚመጡ ገበሬዎች በሚገኙበት አካባቢ እንደሚሄድና የእነርሱን የንግግር ዘዬ ደስ እያለው ይከታተለው እንደነበር ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ አብርሃም እንደ ጠጅ ቤት፣ ጠላ ቤት ያሉ ቦታዎች እየሄደ እዚያ አካባቢ የሚወሩ ወጎችን ይከታተል ነበር።

አብርሃም ለአገሩ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለውም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይናገር ነበር። ለምሳሌ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ምንም ሳይኖርህ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ቦንድ ገዝተሃል መባሉ እውነት ነው? ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ እንዲህ ብሎ ነበር።

«አርቲስቶች አባይ ድልድይ ሄደው ቃል ሲገቡ አብሬ ሄድኩ፡፡ ስንመለስ ሳሚ ምግብ ሊጋብዘኝ ሲል የለም ቦንድ ግዛልኝ አልኩት፡፡

ከአርቲስቶች መጀመሪያ ቦንድ የገዛሁት እኔ ነኝ፡፡ እንዲያውም ልጅ ቢኖረኝ ጀምስ ቦንድ አብርሃም እለዋለሁ ብዬ ነበር፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመናገራቸው በፊት መነባንብ አውጥቼ ነበር፡፡

ማጀታችን ሞልቶ

አልፎ ተርፎ እጃችን ለሌላ እንዳልቸረ

ዛሬ ሁሉም ተቀምጦ

ሌላው ይቅርና ውሃ እንኳ ቸገረ።

እያለ ይቀጥላል፡፡ ከራሴ አገሬን ላስቀድም ብዬ ነው የግድቡን ቦንድ የገዛሁት፡፡»

አብርሃም ሳሚ የሚለው ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፍቅሬን ነው። በጣም የቅርብ ጓደኛው እንደነበርና ወደኪነ ጥበብ ስራ እንዲቀላቀል ትልቅ እገዛ እንዳደረገለት አብርሃም ይናገር ነበር። በኪነ ጥበብና በኮሜዲ ስራዎቹ እያዝናና ሲያስተምር የነበረው አብርሃም አስመላሽ በመጨረሻም በፅኑ ታሞ የአልጋ ቁራኛ ሆነ። ከአንድ ዓመት በላይ በሕክምና እየታገዘ በህመም ቆይቶ በተወለደ በ48 ዓመቱ ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። እነሆ በስራዎቹ ግን በአድናቂው ሕዝብ ልብ ውስጥ ይኖራል።

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ

 

  

Related Topics