የተጫሙት ጫማ ባሉበት አካባቢ እንዳይሳቀቁና ዘና ብለው እንዲውሉ የማድረ

መጥፎ የእግርና የጫማ ጠረንን ለማስወገድ

 

 

 

ከመልካም አቀራረብ እና ገጽታ ባለፈ አለባበስዎ እና በዕለቱ የተጫሙት ጫማ ባሉበት አካባቢ እንዳይሳቀቁና ዘና ብለው እንዲውሉ የማድረግ አቅም አላቸው።

አንዳንድ ሰዎች የዋሉበት ቦታ ወይም የነበሩበት ሁኔታ አስገድዷቸው የሰውነታቸው ጠረን ይቀየራል፤ ከዚህ ባለፈ ግን የተጫሙት ጫማ አካባቢያቸው ያለን ሰው ምቾት ሲነሳም ይስተዋላል።

እንደ ቀልድ ችላ የሚባል ግን በማህበራዊ ህይዎት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የሚያሳርፈው ይህ መጥፎ የእግር ጠረን ለባለቤቱ ባይታወቅም አጠገቡ ያለን ሰው በመጥፎ ሽታ ምቾት ይነሳዋል።

በእግር እና በጫማ ውስጥ በሚፈጠር ከፍተኛ ሙቀት እና የእግር ቁስለት ፣ ባክቴሪያ፣ ለእግር የማይስማሙ የካልሲ ምርቶች እና ጫማዎችን መጫማት ለዚህ ችግር እንደ መንስኤ ይወሰዳሉ።

ታዲያ ይህን ከሰው የሚያቆራርጥ መጥፎ የእግር እና የጫማ ጠረን እንዴት መከላከል እንዳለብዎት ከዚህ በታች ያሉትን መፍትሄዎች ይመልከቱ።

 

መፍትሄዎች ለእግር፤

ቤኪንግ ሶዳ፥ አንድ የሾርባ ማንኪያን ቤኪንግ ሶዳ በእጅ ማስታጠቢያ ግማሽ ለብ ያለ ውሃ መቀላቀል እና እግርን እስከ 20 ደቂቃዎች ድረስ መዘፍዘፍና ከዛ አድርቆ መተኛት፤ ይህን ለአንድ ተከታታይ ሳምንት ማድረግ መልካም ነው።

የእንግሊዝ ጨው፥ ሁለት የሾርባ ማንኪያ የእንግሊዝ ጨው በአነስተኛ ባልዲ ውሃ መቀላቀልና ማሟሟት ቀጥሎም እግርን እስከ 15 ደቂቃዎች ያህል በውህዱ ውስጥ መዘፍዘፍና አናፍሶ ደረቅ ሲል መተኛት።

የሻይ ቅጠል፥

 ሁለት ጥቅል የሻይ ቅጠሎችን በሶስት ብርጭቆ ውሃ ማፍላት እና ከፈላ በኋላ በማውጣት፥ ከዛም በግማሽ ባልዲ ውሃ ቀዝቀዝ ማድረግ እና የውሃ ሙቀቱ ለእግር ተመጣጣኝ ከሆነ እግርን ዘፍዝፎ ከ15 እስከ 20 ደቂቃዎች ማቆየት እና ለሳምንት ያህል ይህን መደጋገም።

ዝንጅብል፥

 መካከለኛ ቁመት ያለውን ዝንጅብል በመቆራረጥ እና ለ15 ደቂቃዎች ያህል ውሃ በመጨመር ማፍላት፥ ቀጥሎም ፈልቶ የወረደው ዝንጅብል ላይ ተወቀጠ የቡና ዱቄት መጨመር።

ከዛም የሁለቱን ውህድ በአግባቡ አማስሎ በመቀላቀል ውስጠኛውን የእግር ክፍል ዘወትር ከመኝታ በፊት ለተከታታይ ሁለት ሳምንት በአግባቡ አዳርሶ ማሸት።

እግርን ለብ ባለ ጨዋማ ውሃ መዝፍዘፍም ሌላው መፍትሄ ነው፤ አንድ ተኩል የሾርባ ማንኪያ ጨውን በአንድ ጆግ ውሃ በማፍላት ቀዝቀዝ አድርጎ እግርን ለ20 ደቂቃ መዝፈዝፍና ይህንንም ለሁለት ሳምንታት ያህል መሞከር።

ከበቆሎ የተዘጋጁ የአሲድ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ዘይት መሰል ፈሳሽ ኬሚካሎችም ለዚህ ችግር መፍትሄ ናቸው፤ እግር ላይ የሚከሰትን አላስፈላጊ እርጥበትና ላበት በማስወገድ ጤናማ ያደርጉታልና።

ሽንኩርት፣ አነስ ያሉ አራት ራስ ሽንኩርቶችን ልጦ በስሱ መጨቅጨቅ፤ ቀጥሎም በደንብ ታጥቦ የፀዳው እግርዎ ላይ በጨርቅ በማድረግ ማሰር እና ከሶስት ሰአታት በኋላ በመፍታት ማናፈስ።

አልኮል፣ እግርን በደንብ ታጥቦ ማፅዳት እና ማደራረቅ ቀጥሎም የተወሰነ አልኮልን ውስጠኛው እግር ላይ በማፍሰስ ማዳረስ እና ማሻሸት በደንብ ሲደርቅም እግርን አናፍሶ ከደቂቃዎች በኋላ ጫማ ማድረግ።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት መፍትሄዎች እግርዎን ከማንኛውም የባክቴሪያ እና የፈንገስ ክምችት የመከላከል እና ምናልባት የተፈጠረ መጥፎ ጠረን ካለም ያንን ለማስወገድ የሚረዱ ናቸው።

 

 

መጥፎ ጠረን ላለው ጫማ፥

ሁለት አነስተኛ ጥቅል ቤኪንግ ሶዳን ጫማዎ ውስጥ ማስቀመጥ፥ ውህዱ ሽታውን መጦ እስኪያጠፋው ድረስ ጫማዎን አለመጠቀም።

ወይም ደግሞ ጫማው ውስጥ የቤኪንግ ሶዳውን መበተንና ሌሊቱን ሙሉ ባለበት እንዲቆይ ማድረግ እና ጠዋት ጫማዎን ከማድረግዎት በፊት ቤኪንግ ሶዳውን ማስወገድ።

ጫማውን አደራርቀውና በአልኮል የተነከረ ስፖንጅ ወይም ቀጠን ያለ አሮጌ ፎጣን ተጠቅመው ጫማው ውስጥ ማስቀመጥ ለተወሰነ ጊዜ በዛ መልኩ ማቆየት፥ ቀጥሎም ጫማዎን ማደራረቅ እና አናፍሶ መጠቀም።

ከዚህ ባለፈም 4 ተነክረው የወጡ የሻይ ቅጠል ጥቅሎችን ያስቸገረዎት ጫማ ውስጥ ለአንድ ሌሊት አስቀምጦ ማውጣትና ጫማውን አደራርቆ መጠቀምም ይቻላል።

ይህን ሲያደርጉ ጫማው ውስጥ የተፈጠረው አላስፈላጊ እና አስቸጋሪ ሽታ ከላይ በተጠቀሱት ውህዶች አማካኝነት ተመጦ መውጣት እና መስተካከል ይጀምራል።

ከዚህ ባሻገር ግን ጫማን ቶሎ ቶሎ እና በአግባቡ ማጽዳት፣ ካልሲን በየጊዜው መቀየያር እና ማጽዳት፣ አንድን ጫማ በተለይም ደግሞ ካልሲን ከአንድ ቀን በላይ አለማድረግ።

ሁል ጊዜ የሚያደርጉትን ሽፍን ጫማ መቀየር እና ሰንደል ወይም ክፍት ጫማዎችን መጫማት እና መጠቀም ከሚፈጠር የእግር ውስጥ ሙቀት እና ላብ እና ያንን ተከትሎ ከሚመጣ አላስፈላጊ ሽታ እና መጥፎ ጠረን ለመዳን ይረዳል።

ከናይለንና ፖሊስተር የተሰሩ የካልሲ ምርቶችም ለዚህ ችግር መንስኤዎች ናቸውና ባለሙያዎች አይጠቀሟቸው ሲሉም ይመክራሉ።

እናም በደረሱበት ቦታ ጫማዎን አውልቀው እና ቀለል ብሎዎት መዝናናት እና መጫዎት ፈልገው ባለው አመል ምክንያት ፍላጎትዎን እንዳይገድቡ መፍትሄወቹን በአግባቡ ይጠቀሙባቸው።

source: FBC