ተዋናይ ፍቃዱ ተ/ማርያም የአራት የተለያዩ ነገሥታትን ገጸ-ባህሪ መጫወቱን

ተዋናይ ፍቃዱ ተ/ማርያም የአራት የተለያዩ ነገሥታትን ገጸ-ባህሪ መጫወቱን ያውቁ ኖሯል?

 

Image result for ተዋናይ ፍቃዱ ተ/ማርያም

 

ፍቃዱ ተክለማርያም በ1948 ዓ.ም.  አዲስ አበባ ውስጥ በአራት ኪሎ አካባቢ ተወለደ፡፡ ሚያዚያ 27 አና አጼ ናዖድ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች አስከ ዘጠነኛ ክፍል ተማረ፡፡ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ተስፋዬ አበበ መስርተውት በነበረው የቲያትር ዕድገት ክበብ ውስጥ አባል በመሆን መሳተፍ ቀጠለ፡፡ በትወና እንቅስቃሴውም እየታወቀ መጣና በ1967 ዓ ም በአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ ቅርብ ጓደኛው በነበረው ከሱራፌል ጋሻው ጋር የመቀጠር እድል አጋጠመው:: ፍቃዱ ላለፉት 33 ዓመታት በመድረክ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌሺዥን እና አሁን ደግሞ በፊልም በርካታ ሚናዎችን እየወከለ ተጫውቷለ፡፡ ፍቃዱ በአብይነት ከተሳተፈባቸው ወጥና ትርጉም ተውኔቶች መካከል፦

 

ኦቴሎ፣ ኤዲፐስ ንጉሥ፣ ሐምሌት፣ ቴዎድሮስ፣ ንጉሥ ኦርማህ፣ መቃብር ቆፋሪውና የሬሣ ሳጥን ሻጩ፣ የሰርጒ ዋዜማ፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ ባለካባ ባለዳባ፣ መልዕክተ ወዛደር እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ::

 

ፍቃዱ በቴሌቪዥን ከተወናቸው ተውኔቶች መካከል ያልተከፈለ ኦዳ፣ ያበቅየለሸ ኑዛዜ፣ ባለጉዳይ እና የመሳሰሉት በህዝብ ዘንድ አድናቆትን ያተረፉለት ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ፍቃዱ “መጽሃፍት ዓለም” ይባል በነበረው የሬዲዮ ፕሮግራም “ሞገደኛው ነወጤ፣ ጥቁር ደም፣ ሳቤላ፣ የነበረው እንዳልነበር” የተባሉትን አጭርና ረጅም ልቦለዶችን ተውኔታዊ መልክ በመስጠት ቀልብን በሚይዝ የአተራረክ ስልት አቅርቧቸዋል፡፡ ፍቃዱ አሁን አሁን እየታወቀ የወጣው ከመድረክ ይልቅ በፊልም ሥራዎች ላይ ነው፡፡ ከተወነባቸው መካከል አንድ በሆነው “ቀይ ስህተት” በተባለው ፊልም የተዋጣለት ፊልም ለመሥራት በመብቃቱ “አቶዝ” በሚል መጠሪያ የምትታወቀውን መኪና የቴዲ ስቱዲዮ ሽልሞታል::

 

ፍቃዱ በአንድ ወቅት የተለያየ ሰብዕና ያላቸውን  ነገሥታትን ሚናዎች በመጫወቱ ምን እንደሚሰማው እና ከነገስታቱ ማንን መሆን እንደሚመኝ ለተጠየቀው ጥያቄ ሲመልስ፣ “መቸም ኤዲፐስ መሆን ፍርጃ ነው፡፡ የሃምሌትን ንጉስ ገላውዴዎስን መሆንም አልፈልግም:: ባይሆን ቴዎድሮስንና ንጉስ አርማህን ብሆን አልጠላም” ሲል መልሷል:: በተለይ ለዓጼ ቴዎድሮስ ያለውን ክብር ለመግለጽ የሰርጉለት በቴዎድሮስ አደባባይ ተገኝቶ የትያትሩን የተወሰነ ክፍል መነባነብ ላጃቢዎቹ አቅርቦ ነበር::

ምንጭ፡-ሰዋሰዉ

 

  

Related Topics