ቅናት ያለንን ግንኙነት ሊጠቅምም ሊጎዳም እንደሚችል በዘርፉ የተመራመሩ

 ቅናት ለፍቅር ምኑ ነው? (በተለይ በፍቅር ውስጥ ሆነው በአፈቀሩት ላይ የሚቀኑ እንዲያነቡት ይመከራል)

 

ብዙ ሰዎች እርር ድብን ብለን እናውቅ ይሆናል፡፡ በቅናት! ዛሬ እኔ እና እናንተ ስለ ቅናት ልናወጋ፣ በቅናት ያረርንባቸውን ጊዜያቶች በድጋሚ ልናጤን ነው፡፡ የእናንተን አላውቅም እንጂ እኔ በበኩሌ ከዚህ ቀደም የኔው ጉድ በቅናት አንፃር ያደረገችበትን ቀኖች በምናቤ እንደ ፎቶ አልበም ደርድሬያቸዋለሁ፡፡ መቼም ቀንቼ አላውቅም አትሉኝም፡፡ ቅናት መጠኑ ይብዛም ይነስም የሁላችንንም ልብ ያንኳኳል፡፡ ቅናት እና እሳት ቤት አይዘሉም፡፡ እርግጥ ነው ቅናት ውስጣችን አስደሳች ስሜት የሚፈጥር አለመሆኑን እናውቃለን፡፡ ከዚህ አኳያ ቅናትን ከአሉዊ ስሜቶች ተርታ ልንፈርጀው እንችላለን? ወይንስ ለትዳር አጋራችን ወይንም ለፍቅር ጓደኛችን ያለን ፍቅር ኃያል መሆኑን ማረጋገጫ አድርገን እንወስደዋለን? ከሁሉ በፊት ግን ስለምንወያይበት ርዕስ ግልፅ የሆነ መረጃ ሊኖረን ይገባል፡፡ ለዛም ነው ቀድመን ቅናት ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያለብን፡፡

ቅናት ምንድነው?

 

ቅናት ማለት በተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ውስጥ እያለን በተለያዩ ምክንያቶች በውስጣችን ሊፈጠር የሚችል፣ የምንወደውን ሰው ከማጣት ጋር የተያያዘ የስጋት እና ሽብር ስሜት ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ይሄ የሽብር ስሜት ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ይሄ የሽብር ስሜት በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላል፡፡ በተጨማሪም ቅናት ያለንን ግንኙነት ሊጠቅምም ሊጎዳም እንደሚችል በዘርፉ የተመራመሩ ሰዎች ገልፀዋል፡፡

አሉታዊ ቅናት

ቅናትን አሉታዊ የምንልበት ዋናው ምክንያት በዓለም ላይ ከተፈፀሙ የትዳር ጓደኛ ግድያ መንስኤዎች መካከል ቅናት ፊት አውራሪ ሆኖ በመምራት ላይ ስለሚገኝ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ቅናት ልክ የማይኖረው ከሆነ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል፡፡

ቅናትን አሉታዊ ቅናት የምንለው መቼ ነው? ቅናት ከልክ እንዳለፈ ለማረጋገጥ የተወሰኑ ምልክቶችን ልጠቃቅስ፡፡

ሀ. የቅናት ስሜት በሚፈጠርበት ወቅት ስሜታችንን ለመግለፅ ቃላትን ሳይሆን ጉልበትን መጠቀም ስንጀምር፤ በግልፅነት ከመወያየት ይልቅ ቅናት እንዲያድርብን አደረግን የምንለው ሰው ላይ ለዱላ ስንጋብዝ፡፡

ለ. የትዳር አጋርህ/ሽ፣ ጓደኛህ/ሽ ካንተ/ካንቺ ጋር በሌለ/ች ሰዓት ጊዜህን/ሽ ‹‹ምን እያደረገ/ች ይሆን?›› በማለት ቀኑን ሙሉ የምንብሰለሰል ከሆነ አልፎ ተርፎም ቀኑን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም ኮርኒስ እየቆጠርን ነገር የምንበላ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡

ሐ. የቅናት ስሜት ከፍቅር የመነጨ ሳይሆን እምነት ከማጣት የመጣ ሲሆን፤

መ. የትዳር አጋርህ/ሽ ውሎውን/ዋን ለመናገር ወይም አንተ/አንቺ በሌለህበት/ሽበት ሰዓት የተፈጠሩ ነገሮችን ለመናገር የምትሳቀቅ/ቂ ከሆነ፤

ሠ. በዚህ በመዘዘኛ ቅናት ምክንያት ለምግብ ያለን ፍላጎት ከቀነሰ፤ ጭንቀት ውስጥ ከገባን፤ የልብ ምታችን በተደጋጋሚ የሚጨምር ከሆነ፣ ከልክ በላይ የሚያልበን እንዲሁም ቶሎ የሚደክመን ከሆነ፤

ረ. በመጨረሻም ቅናት ከፍቅረኛችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ላይ ክፍተት እየፈጠረ ከመጣ ችግር አለ ማለት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሊንዳ ብሎር የምትባል ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት ቅናታችን አሉታዊ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ እነዚህን ሶስት ጥያቄዎች ራሳችሁን ጠይቁ ትለናለች፡፡

1. ይሄ ቅናት የዕለት ተዕለት ኑሮአችሁ ጋር እየተጋጨ ነው?

2. የምወደውን ሰው እያሳዘነ እና እየጎዳ ነው?

3. ቅናቱ እኔ ከምቆጣጠረው በላይ እሱ ይቆጣጠረኛል?

ከላይ ለተዘረዘሩት ሶስት ጥያቄዎች መልሳችሁ ‹‹አዎን›› ከሆነ ጉድ ፈልቷል ማለት ነው ትላለች የሳይኮሎጂ ባለሙያዋ፡፡

እንግዲህ ወዳጆች ከላይ የጠቀስኳቸው ነገሮች በተደጋጋሚ በፍቅር ግንኙነትሽ/ህ ጊዜ የሚከሰቱ ከሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በአቅራቢያችን ወደሚገኝ የስነ ልቦና አማካሪ ብንሄድ መፍትሄ ልናበጅለት እንችላለን፡፡ አሊያም ማማከሩ ለውጥ ካላመጣ በሰላም መለያየቱ ሁሉ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡

አዎንታዊ ቅናት

ቅናት በአብዛኛው ግንኙነቶች አደጋ ላይ ሲጥል ብንመለከተውም መጠኑ ሳይበዛ ግን አዎንታዊ ጎኑ ሊያመዝን የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ታዲያ አዎንታዊ ቅናት ስል ደስ የሚል ስሜት የሚፈጥር ቅናት ማለቴ እንዳልሆነ ይገባችኋል፡፡ ታዲያ ቅናትን አዎንታዊ የምንለው እንዴት ነው?

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያትቱት መጠነኛ ቅናት በፍቅር ጓደኛ ላይ ደስ የሚል ስሜት ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም የፍቅር ጓደኛችንን ምን ያህል እንደምንወድ ሊያሳይ ይችላል፡፡ የፍቅር ወይም ትዳር አጋራችን መጠነኛ ቅናትን እንደ ፍቅር መገለጫ ሊመለከቱት ይችላሉ፡፡ ይሁን እጂ ብዙ ጥንዶች የተሰማቸውን ደስ የሚል ስሜት ቅናት ላደረበት አጋራቸው ሲያካፍሉት አይስተዋልም፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ መግባባት ባለመቻል እና ንትርክ መካከላቸው ያለው የፍቅር ድባብ የተጋረደባቸው ጥንዶች መጀመሪያ በፍቅር ሲወድቁ ለፍቅረኛቸው የነበራቸው ወይንም ስለ ፍቅረኛቸው የሚወዱትን ጎን መልሶ ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት ፍቅረኛቸውን ከሌላ ሰው ጋር ቢመለከቱት/ቷት በሚፈጠርባቸው የቅናት ስሜት ያ ጠፍቶ የነበረ የጠብ ምክንያት ግልጽ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከዛ ሰው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያድሱ ያስገድዳቸዋል፡፡ ከንትርክ የበለጠ ጥሩ የጋራ ታሪክ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ፡፡ ያንንም ጥሩ ጊዜ ለመመለስ የሚያስችል አቅም ያገኛሉ፡፡ ‹‹በእጅ ያለ ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል›› እንዲሉ ነው ነገሩ አንዳንዴ፡፡

የቅናት መንስኤዎች

ቅናት አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት ሁሉ መንስኤዎቹም የተለያዩ ናቸው፡፡ የቅናት መንስኤ በተለይ ቅጥ ያጣ ቅናት መነሻው የፍቅር አጋራችን ላይ ከመጠን ያለፈ ጥገኛ መሆን እና በራስ መተማመን አለመቻል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሁሉም አፍቃሪ ቅናት መንስኤ ጥገኛ መሆን እና በራስ መተማመን አለመቻል አይደለም፡፡ አንዳንድ ድርሳኖች እንደሚያስነብቡን አዎንታዊ ቅናቶች ኃያል ከሆነ ፍቅር ሊመጣ እንደሚችል እና መንስኤውም ፍቅረኛችን ካላት/ካለው የሶስተኛ ወገን ግንኙነት ጋር ሳይሆን ሌሎች ግዑዝ ከሆኑ ነገሮች ጋር በተያያዘ ሁሉ ሊመጣ ይችላል፡፡ ለአብነት ያህል ፍቅረኛ ሆዬ በስራ ብዙ ሰዓቱን/ቷን የሚያሳልፍ/የምታሳልፍ ሲሆን ወይንም ብዙ ጊዜውን/ዋን በማንበብ የምታሳልፍ/የሚያሳልፍ ከሆነ አዎንታዊ የምንለው አይነት ቅናት ሊያድርብን ይችላል፡፡ ቅናቱም የፍቅር ግንኙነቱን የሚያቀጭጭ አይነት ቅናት አይደለም፡፡ ጊዜ ከመፈለግ ጋር የሚያያዝ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቅናት መንስኤ አሁን ካላቸው ግንኙነት በፊት በነበራቸው ግንኙነት የተከዱ ወደፊት በሚኖራቸው ግንኙነት የቅናት ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል፡፡ ይህ ቅናት በበኩሉ በአመዛኙ ከእምነት ማጣት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

አሉታዊ ቅናትን ለማስወገድ

‹‹እርር ድብን ማለት አንገሽግሾኛል፤ ጨጓራዬን ልተፋው ነው፤ አንድ በሉኝ›› የሚሉ ከሆነ ደግሞ ቅናትን ፈፅሞ ልናጠፋው ባንችል እንኳ እንዴት ልንገራው እንደምንችል እንመልከት፡፡

1. መፍትሄው ብዙ ጊዜ ያለው እዛው ፍቅረኛችን እጅ ስለሆነ የሚስማማንን ስሜት ለፍቅረኛችን ግልፅ ማድረግ ይመከራል፡፡

2. ምክንያታዊ ለመሆን መሞከርም ጥቅም አለው፡፡ ለምን በሉኝ? ብዙ ጊዜ ቅናት ያሳደረብን ጉዳይ የሚጨበጥ ነገር ላይሆን፣ ጨርሶ ያልታሰበና ያልተፈጠረ የእኛ አዕምሮ ብቻ ያውጠነጠነው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የሚያስቀናንን ጉዳይ ከእውነታው ጋር በማስተያየት፣ ምክንያታዊ ለመሆን በመጣር የሚስማማንን ስሜት መርምረን ልንገራቸው እንችላለን፡፡

3. ለራሳችን ያለን ክብር ሊጨምር ይገባል፡፡ በራስ መተማመናችንን ከፍ ያደርጋሉ የምንላቸውን የሌሎችን በራስ መተማመን የማይነኩ ነገሮችን ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ አለ አይደል እኛ ከፍ ብለን እንድንታይ ሌላው ዝቅ ማለት የለበትም፡፡ ሌላውን ዝቅ ሳያደርጉ እኛን ከፍ የሚያደርጉ ነገሮችን ማድረግ በራስ መተማመናችንን ይጨምራል፡፡

4. ፍቅረኛሞች በአመለካከት ስለሚለያዩ ከሶስተኛ ወገን ጋር ያላቸው የግንኙነት ገደብ ይለያያል፡፡ ስለዚህ የኛን ገደብ ባለማወቅ ፍቅረኛችን ልታስቀይመን/ሊያስቀይመን ትችላለች/ይችላል፡፡ በመሆኑም አስቀድመን የሚመቹንን እና የማይመቹንን ከሶስተኛ ወገን ጋር ያሉ ግንኙነቶች ግልፅ ማድረግ መልካም ነው፡፡

ምንጭ፡- ትኩስ ነገር

 

 

  

Related Topics