ጭንቀት በወንዶችና በሴቶች አእምሮ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የተለያየ ነው

ጭንቀት በወንዶችና በሴቶች አእምሮ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የተለያየ ነው ተባለ

 

በጣም ከሚያሳቅቁ ወይም አእምሮን ከሚረብሹ ከስተቶች በኋላ የሚከሰት ጭንቀት የወንዶች እና የሴቶች አእምሮ ላይ በተለያየ መልኩ ጉዳት እንደሚያደርስ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ጥናት አመለክቷል።

ጥናቱ በሴቶች ላይ አእምሮን በጣም የሚያሳቅቅ ወይም ሚረብሽ ነገር በሚያጋጥምበት ጊዜ “ኢንሱላ” የተባለውና ስሜትና ችግርን የሚመለከት እንዲሁም የሚለካ የአዕምሮ ክፍል በመጠኑ እንደሚያንስ አመልክቷል።

በአንጻሩ የወንዶች የእምሮን የሚያሳቅቅ ወይም የሚረብሽ ነገር በሚያጋጥምበት ጊዜ “ኢንሱላ”የተባለው የአዕምሮ ክፍል ከተለመደው መጠን በላይ ጨምሮ ይገኛል የሚለውም በጥናቱ ላይ ተቀምጧል።

ይህም በጣም የሚያሳቅቅ ወይም የሚረብሽ ነገር በሚያጋጥምበት ጊዜ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ለምን ለጭንቀት እንደሚጋለጡ ያመለክታል ይላሉ ተመራማሪዎቹ።

የጥናቱ ውጤትም ሴቶች እና ወንዶች የሚያስደነግጡ ወይም የሚያሳስቡ ነገሮች ካጋጠማቸው በኋላ የሚታይባቸው የጭንቀት መጠን የተለያየ መሆኑን ያሳያል ሲሉም ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።

ይህ ደግሞ ለወንዶችም ይሁን ለሴቶች ሊደረግ የሚገባ ህክምና እንደ ውጤቱ ሊለያይ እንደሚገባ ያመለክታል ብለዋል።

ከአሜሪካ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተወጣጡት የጥናት ቡድኑ አባላት እንደሚናገሩት፥ ከአሰቃቂ ክስተት በኋላ ለጭንቀት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች “ኢንሱላ” የተባለው አእምሮ ክፍላቸው ከእድሜያቸው ቀድሞ ያረጃል።

“ኢንሱላ”፥አእምሯችን የህመም ስሜቶችን የሚለይበት ስፍራ ሲሆን፥ በአእምሯችን ውስጥ የሚገኝ፣ ውስብስብ እና ከመላው አካላችን ጋር በርካታ ግንኙነት ያለው መሆኑንም ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ።

ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው ላይ እድሜያቸው ከ9 እስከ 17 የሆኑ ወንድ እና ሴቶች የአእምሮ ሁኔታን በመከታተል ነው ያካሄዱት።

የጥናቱ ተሳታፊዎችን በሁለት ቡድን የከፈሉ ሲሆን፥ አንደኛው ቡድን ላይ 14 ሴቶች እና 16 ወንዶች እንዲሁም በሌላኛው ቡድን ላይ ደግሞ 15 ሴቶች እና 14 ወንዶችን ተጠቅመዋል።

14 ሴቶች እና 16 ወንዶች ያሉበት ቡድን በጣም አስቃቂ እና አስደንጋጭ ነገር ላለበት ነገር እንዲጋለጡ ያደረጉ ሲሆን፥ ሁለተኛው ቡድን 15 ሴቶች እና 14 ወዶች ያሉት ደግሞ ከሚያስደነግጡ ነገሮች እንዲርቁ አድርገዋል።

በዚህም የሁለቱም ቡድን ተሳታፊዎች የኢንሱላ መጠን የታየ ሲሆን፥ ለሚያስደነግጥ ወይም ለሚያሳቅቅ ነገር የተጋለጡት ወንዶች እና ሴቶች የኢንሱላ መጠን ላይ ለውጥ መታየቱ ነው የተነገረው።

ይህም ለሚያሳቅቁ ነገሮች ተጋላጭ የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች መጠኑ ቢለያይም ኢንሱላ በተባለው የአአምሮ ክፍል ላይ የተለያየ የመጠን ችግር ያስከትላል ተብሏል።

በጣም ከሚያሳቅቁ ከስተቶች በኋላ የሚመጣ የአእምሮ ጭንቀት ምንድን ነው…?

በጣም ከሚያሳቅቅ ክስተት በኋላ የሚከሰት የአእምሮ ጭንቀት፥ ከከፍተኛ የተሽከርካሪ አደጋ በኋላ፣ ከተፈጥሮ አደጋ በኋላ እንዲሁም ለተለያዩ አስደንጋጭ እና አሰቃቂ አደጋዎች በኋላ የሚከሰት የጭንቀት አይነት ነው።

 

ምልክቶቹም፦

ክስተቱን በአዕምሯችን ደጋግሞ መመልከት እና በህልማችን ማየት

እንቅልፍ ማጣት

ምግብ በአግባቡ አለመመገብ

ራስን ዘና አለማድረግ ናቸው ተብሏል።

እንዲህ አይነት ችግሮች በተለይ በወጣቶች ላይ ሊከሰት ይችላል የተባለ ሲሆን፥ ክስተቱም ለአንድ ሳምንት አልያም ለአንድ ወር ሊቆይ እንደሚችል ነው ተመራማሪዎች የሚናገሩት።

እንዲህ አይነት የጭንቀት ችግር ያለባቸው ሰዎች የአእምሮ ጤና ባለሙያዎችን ቢያማክሩም መልካም ነው ይላሉ።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

 

  

Related Topics