የአልኮል መጠጥ የወንዶችን የዘር ፍሬ ይጎዳል

 

የአልኮል መጠጥ የወንዶችን የዘር ፍሬ ይጎዳል

 

 


የመውለድ አቅምን ይቀንሳል ተብሏል የአልኮል መጠጥ የሚወስዱ ወንዶች የዘር ፍሬያቸው በመጠንና በጥራት እንደሚቀንስና በመውለድ አቅማቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ጥናት አመለከተ፡፡ “ብዙ ጥናቶች የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ መውሰድ በአጠቃላይ ለጤና እንደማይበጅ አረጋግጠዋል፡፡
አልኮል በመጠኑ መውሰድ በሥነተዋልዶ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው የሚያሳይ ጥናት እምብዛም የለም” ይላሉ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ት/ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ማይክል ኢሰንበርግ፡፡ በሳምንት 40 ብርጭቆ ወይም ከዚያ በላይ የአልኮል መጠጥ የሚወስዱ ወንዶች የዘር ፍሬያቸው እጅግ በጣም እንደሚቀንስ ጥናቱ ቢያረጋግጥም፤ ጥናት አድራጊዎቹን ያስገረማቸው ሌላም ነገር አለ፡፡ በሳምንት አምስት ብርጭቆ የአልኮል መጠጥ (ቢራ ወይም የወይን ጠጅ ሊሆን ይችላል) ብቻ የሚጠጡ ወንዶች ላይም ተመሳሳይ ችግር እንደተስተዋለ በሳውዘርን ዴንማርክ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና የጥናቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ቲና ኮልድ ጄንሰን ተናግረዋል፡፡
በጥናቱ አካሄድ የተነሳ በወንዶቹ የዘር ፍሬ ላይ የታየው ለውጥ በአልኮል መጠጡ ሳቢያ የመጣ ይሁን አይሁን ለማወቅ አልተቻለም ይላሉ - አጥኚዎቹ፡፡ “ለዘር ፍሬው በቁጥርም ሆነ በጥራት መቀነስ እንደ ምግብ፣ ሲጋራ፣ የሰውነት ክብደት ወዘተ… ያሉ ሌሎች ነገሮች ጋር ለማያያዝ ብንሞክርም ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር አላገኘንም፡፡ ችግሩ ከአልኮል መጠጣት ጋር በተያያዙ ሌሎች ጉዳዮች ሊከሰት ይችላል የሚለውን ግን ውድቅ አላደረግነውም” ብለዋል ጄንሰን፡፡ ጥናቱ ለውትድርና አገልግሎት ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ የጤና ምርመራ ያደረጉ ከ1 ሺ 200 በላይ የዴንማርክ ወጣት ወንዶችን ያካተተ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 28 የሚደርስ ነው፡፡
የአልኮል መጠጥ ልማዳቸውን የተመለከተ መጠይቅ እንዲሞሉ ከመደረጋቸውም በተጨማሪ የዘር ፈሳሽ ናሙናና ደም ሰጥተዋል፡፡
ከምርመራው በተገኘው ውጤትም በየሳምንቱ አንድ ብርጭቆ አልኮል ከሚጎነጩት ይልቅ በየሳምንቱ አምስት ብርጭቆ የአልኮል መጠጥ የሚወስዱት የዘር ፍሬያቸው በመጠንም፣ በጥራትም፣ በጤነኝነትም እጅግ ዝቅ ያለ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በሳምንት ቢያንስ 25 ብርጭቆ አልኮል የሚጨልጡ ወንዶች፤ የዘር ፍሬያቸው በመጠንም ሆነ በጥራት በእጅጉ ያሽቆለቆለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሳምንት 40 ወይም ከዚያ በላይ በሚጠጡ ወንዶች ላይ በተካሄደው ጥናት፤ በሳምንት እስከ 5 ብርጭቆ ድረስ ከሚጠጡት በ33 በመቶ ያነሰ የዘር ፍሬ ይዘት እንደነበራቸው ታውቋል፡፡ “ብዙ ወንዶች ዝምተኛ ጠጪዎች ናቸው፤ ይሄ ባህርያቸው እንደሚጎዳቸው ግን አይገነዘቡም፡፡ ዝምተኝነታቸው ከሚፈልጉት በላይ እንዲጠጡ ያደርጋቸዋል” ያሉት ደግሞ በሂዩስተን በሚገኝ ሆስፒታል የማህጸንና የወሊድ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ማይክል ኸርድ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ስካር ሆርሞኖችንና በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኬሚካሎችን (ኮርቲሶል፣ ግሉኮስ፣ ኢንሱሊንና የወንድ ሆርሞን) እንዲለወጡ ያደርጋቸዋል፡፡ “እኒህ ሁሉ የዘር ፍሬ ጥራት ላይ ችግር ያስከትላሉ፤ ጥራቱ ዝቅ ያለ የዘር ፍሬ ደግሞ ፅንስ የማፍራት ሂደቱን ሊያስተጓጉለው ይችላል” ብለዋል ኸርድ፡፡
source: ጤና24

 

  

Related Topics