ተዋናይትና ዳይሬተተር አርቲስት ሰብለ ተፈራ (እማማ ጨቤ)

 

 አርቲስት ሰብለ ተፈራ 

 

 

እኔም እግዚአብሔር አምላክ የአርቲስቷን ነፍሷን በገነት ያኑር እያልሁ የስኬት ምሳሌ ስለሆነች ወጣቶች የህይወት ተሞክሮዋን ይማርበት ዘንድ እንደሚከተለው ጽፌዋለሁ።

 

ተዋናይትና ዳይሬተተር አርቲስት ሰብለ ተፈራ (እማማ ጨቤ) በአዲስ አበባ ከተማ ወሎ ሰፈር በተለይም አይቤክስ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ግንቦት 18 ቀን 1968 ዓመተ ምህረት ተወለደች።አርቲስት ሰብለ ተፈራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ትምህርት ቤት የተከታተለች ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች።አርቲስት ሰብለ ተፈራ ለደረሰችበት የኪነ ጥበብ ህይወቷ ከ14 ዓመቷ ጀምሮ ከፍተኛ ጥረት ታደርግ ነበር። በ1984 ዓመተ ምህረት በክቡር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበባ የቲያትር ጥበብ ስልጠናም ወስዳለች።በመጀመሪያም "ጭንቅሎ" የተሰኜውን የትያትር ስራዋ በማቅረብ የትወና ብቃቷን በሚገባ አስመስክራለች። አርቲሰስት ሰብለ ተፈራ የትወና ተሰጦዋን ለማሳደግ የትያትር ጥበባት ትምህርቷን ተከታትላ በወጋገን ኮሌጅ ዲፕሎማዋን ያገኘች ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል የዲግሪ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ነበረች።አርቲስት ሰብለ ተፈራ ከ30 በላይ ትያትሮችን በመስራት የዛሬዋን ኤርትራን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ያቀረበች ሲሆን በአገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመሳተፍም በተዋናይነት ከ20 በላይ ፊልሞችን በተለየ ብቃት ችሎታዋን አሳይታለች።ከተወነችባቸው ትያትሮች መካከልም አምታታው በከተማ፣ 12 እብዶች በከተማ፣ ጓደኛሞቹ፣ ወርቃማ ፍሬ፣ ሰቀቀን፣ ህይወት በየፈርጁ፣ የሰርጉ ዋዜማ፣ ላጤ፣ እኩይ ደቀ መዝሙር፣ አንድ ቃል፣ የክፉ ቀን ደራሽ፣ እንቁላሉ፣ አብሮ አደግ፣ ሩብ ጉዳይና ሌሎች ትያትሮች ይገኙበታል።ከተወነችባቸው ፊልሞች መካከል ደግሞ ፈንጂ ወረዳ፣ ያረፈደ አራዳ፣ ማግስት፣ ትንቢት የሚሉ ፊልሞች በአድናቂወቿ ዘንድ ሁሌም ይታወሳሉ።ጥረቷ ከቀን ወደ ቀን እያደገ የመጣው አርቲስት ሰብለ ተፈራ በከፍተኛ ጥረት እርጥባን የተሰኘውን ትያትር በፕሮዲዩሰርነት ሰርታ በማጠናቀቅ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ በአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ ከአራት ዓመታት በፊት ለእይታ እንዲበቃ ያደረገች ሲሆን በተጨማሪም አልበም የተሰኘውን ፊልም በዋና አዘጋጅነትና ፕሮዲዩሰርነት በማቅረብ ከሁለት ዓመታት በፊት ለህዝብ አሳይታለች።

ከትያትርና ፊልም ትወና ስራዋ በተጨማሪ ለዚሁ ሙያዋ ይሆን ዘንድ ከፍታ ታስተዳድረው በነበረው ሰብለ ፊልም ፕሮዳክሽን በርካታ የሬዲዮና የቴሌቪዠን ማስታወቂያዎችን በመስራት ላይ ነበረች።

አርቲስት ሰብለ ተፈራ በትወና ሙያዋ በአብዛኛው የአገራችን ክልሎች በመዘዋወር ስራዎቻን ያቀረበች ሲሆን ከኢትዮጵያ ውጭም ስራዎቿን በሱዳን አብዬ በኢፌዴሪ የአገር መከላከያ ሰራዊት የሰላም አስከባሪ ሀይል፣ በእስራኤል ሴት ወንድሜ የተሰኘ ትያትር፣ በእንግሊዝ የእኛ እድር የተሰኘ ትያትር፣ በደቡብ አፍሪካና እንዲሁም በቅርቡ የእኛ እድር የተሰኘውን ትያትር በአሜሪካና በሌሎች አዋሳኝ አገራት ለተከታታይ ስድስት ወራት ይዛ በመጓዝ ከስራ ባልደረቦቿ ጋር ስራዋን አቅርባለች።

በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለአምስት ዓመታት በቀረበው "ትንንሽ ፀሐዮች" ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ከታዳሚው አዕምሮ የማይጠፉትን "እማማ ጨቤ" የተሰኜውን ገጸ ባህርይ ወክላ በመጫወት ከፍተኛ ዝናና ፍቅር አግኝታበታለች።በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እየቀረበ በሚገኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የቤት ሰራተኛ የሆነችዋን የትርፌ"ን ገጸ ባህርይ ወክላ በመተወን ላይ ነበረች።

 በእነዚህ ስራዎቿ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የትወና ብቃቷን በማስመስከር ልቃ የወጣችበትና በህዝባችን ዘንድም ከፍተኛ ዝናና ፍቅር ተጎናጽፋበታለች።አርቲስት ሰብለ ተፈራ ከአቶ ሞገስ ተስፋዬ ጋር ሚያዚያ 27 ቀን 1999 ዓመተ ምህረት ትዳር መስርታ በልዩ ፍቅር ትኖር ነበር። አርቲስት ሰብለ ተፈራ በመንፈሳዊ ህይወቷ የተለያዩ በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ በተጠራችባቸው ቦታዎች ሁሉ ማለትም ከ400 በላይ ቦታዎች በመዘዋወር ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ትታወቃለች።ከልጅነቷ ጀምሮ በፀበልና በፍቅር በቤተክርስቲያን ያሳደጋት አምላኳን ቅዱስ እግዚአብሔርን በዝክረ ከሀንና በተለያዩ መንፈሳዊ ማህበራት በአንድነት በመሆን ገዳማትና ቅዱሳትን መካናትን ስታገለግል ኖራለች።በህይወት ከመለየቷ ከ40 ሰዓታት በፊትም ጳጉሜ 5 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት በቱሉ ዲምቱ አቃቂ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት የራሷን "የመዳን ቀን ዛሬ ነው" የሚልና ሌሎች ግጥሞችን አቅርባለች።ለሙያዋ ከፍተኛ ክብር የነበራት አርቲስት ሰብለ ተፈራ ቤተሰቧን አክባሪ፣ በእምነቷ ጠንካራ፣ ሰው አክባሪ፣ ተግባቢ፣ ተጫዋች፣ ፍልቅልቅና ሳቅ የማይለያት ስትሆን ሰውን ለማስደሰትና ለመርዳት ሁሌ ጥረት ስታደርግ የኖረች ቅን ባለሙሉ ተስፋና ለሙያዋ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለች ልዩ የጥበብ ሴት ነበረች።

 ሆኖም መሰከረም 1 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ከቀኑ 10፡40 ላይ ንፋስ ስልክ አካባቢ ከባለቤቷ አቶ ሞገስ ተስፋዬ ጋር በግል ተሽከርካሪያቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ ቆሞ ከነበረ ከባድ መኪና ጋር በመጋጨት በደረሰባቸው አደጋ በተወለደች በ40 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።

 

     ምንጭ፦ተስፋ ያለው ተጓዥ

 

 

 

  

Related Topics